
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12/ 2017 ዓ/ም፡- ከትግራይ ጦርነት የተረፉ ስምንት ሰዎች ለጀርመን ፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ጋር የወንጀል ክስ አቀረቡ። ክሱን ያቀረቡት “የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች” ፈጽመዋል ባሏቸው አስራ ሁለት ከፍተኛ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የመንግስት እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ላይ ነው።
ክሱ የተዘጋጀው በሌጋል አክሽን ዎርልድዋይድ (LAW) እና በዶ/ር አና ኦህሚቼን እንዲሁም በዴቤቮይስና ፕሊምፕተን ኤል ኤል ፒ እና በአውሮፓ ህገመንግስታዊ እና ሰብአዊ መብቶች ማዕከል ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል። የተረበው ክስ በጀርመን ዓለም አቀፍ ዳኝነት ስልጣን መርህ መሰረት ሲሆን “ይህም በውጭ አገር የተፈጸሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ላይ ክስ ለመመስረት ስለሚያችል ነው”።
ሌጋል አክሽን ዎርልድዋይድ (LAW) እንደገለጸው ክሱን ያቀረቡት የቀድሞው የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኛ እና የቀድሞው ጊዜያዊ የመንግስት ባለስልጣንን ጨምሮ ስምንት ከጦርነቱ የተረፉ ሰዎች ናቸው። ድርጅቱ አቤቱታ አቅራቢዎቹ “እንደ ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፤ የጾታ ጥቃት፣ በዘፈቀደ መታሰር፣ ማሰቃየት እና መራብ የደረሰባቸውንና እስካሁን ድረስ ፍትህ የተነፈጉ” መሆናቸውን ገልጿል። አክሎም ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ውስጥ እንደሚኖሩ እና የጀርመን ፌዴራል አቃቤ ህግ ምርመራ እንዲጀምር ጠይቀዋል ብሏል።
እንደ ድርጅቱ ገለጻ፤ ህዳር 2020 በተጀመረው የትግራይ ጦርነት “አስገድዶ ማስራብ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ ማገድ ፣ ጭፍጨፋ፣ ወሲባዊ እና ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ስቃይ እና በዘፈቀደ እስርን” ጨምሮ “አሰቃቂ ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ተከታታይ ክሶች” ቀርበውበታል። በአቤቱታው እንደተገለጸው እነዚህ የመብት ጥሰቶች የተፈጸሙት” በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ኃይሎች እንዲሁም በተባባሪ ሚሊሻ ቡድኖች” በዋናነት በትግራይ ንጹሃን ላይ ነው። ይሁን እንጂ “ሌሎች የጦርነቱ ተሳታፊዎችና ከሌሎች የብሄር የተውጣጡ ሲቪሎችም ተሳትፈዋል” ሲል የጠቀሰው ድርጅቱ፤ “በጦርነቱ የሟቾች ቁጥር ከ300,000 እስከ 800,000” እንደሚገመት “በስፋት የተጠቀሰ ምንጭን” ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር በፈረንጆቹ 2021 የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ፤ ” የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን” ማስረጃዎች በመጥቀስ ዓለም አቀፍ የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቡ ይታወቃል። ጥቅምት 2023 ሥልጣኑ ከማለቁ በፊት ኮሚሽኑ “በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን” በእርግጠኝነት ለመወሰን ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።
በመጋቢት 2023 አሜሪካ፤ በትግራይ ተጀምሮ እና ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተስፋፋው እና ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የጦር ወንጀል በትግራይ ክልል ውስጥ እንደተፈፀመ ገልጻለች።
“ብዙዎቹ እነዚህ ወንጀሎች በዘፈቀደ የተፈጸሙ አይደሉም፣ ወይም የጦርነት ውጤት ብቻ አይደሉም፣ የተሰሉ እና የታሰቡ ናቸው” ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ኃይል አባላት “ግድያን፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች የጾታ ጥቃቶችን ጨምሮ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፈጽመዋል” ያሉት ብሊንከን፣ “የአማራ ኃይሎችም በሃይል በማፈናቀል ወይም በማዛወር በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ድርጊት አከናውነዋል ብለዋል። አክለውም በምዕራብ ትግራይ “የትግራይ ተወላጆችን በመያዝ የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጽመዋል” ብለዋል።
ሌጋል አክሽን ዎርልድዋይድ (LAW) የትግራይ ተጎጂዎች የክስ አቤቱታን ሲያቀርብ ይህ ለሁለተኛው ጊዜ መሆኑን ገልጿል። የመጀመሪያውን ያቀረበው ከፓን አፍሪካ የሕግ ባለሙያዎች ህብረት እና ከአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ቻርተር ስር የተጣለባትን ግዴታ እንደጣሰች ገልጿል።
ድርጅቱ እንዳመለከተው በጥቅምት 2022 የአፍሪካ ኮሚሽን “ኢትዮጵያ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ግድያ መፈጸም እና ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ሁሉንም ጥሰቶች እንድታቆም እና በትግራይ ውስጥ ሰብአዊ ተደራሽነትን እንድታረጋግጥ” አሳስቧል።
በጀርመን የቀረበው አቤቱታ በመጀመሪያ በመስከረም 2024 ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የቀረበ ሲሆን በመጋቢት 20 ቀን 2025 ተጨማሪ ማስረጃዎች ተጨምረዋል። ድርጅቱ የጀርመን የፌዴራል አቃቤ ህግ “በተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ መዋቅራዊ ምርመራ የመክፈት፣ የግለሰብ ምርመራ የማካሄድ፣ የእስር ትዕዛዝ የማውጣት እና ተጠያቂዎችን የማስፈጸም አቅም አለው” ብሏል።አስ