ማህበራዊ ጉዳይዜናፖለቲካ

ዜና: በአብዘሃኛው የአማራ ክልል አከባቢዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ማድረስ አስቸጋሪ ሁኖብኛል ሲል የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19/2017 ዓ.ም፡- በአብዘሃኛው የአማራ ክልል አከባቢዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ማድረስ አስቸጋሪ ሁኖብኛል ሲል የመንግስታቱ ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ትላንት መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ማስተባበሪያ በበርካታ የክልሉ ቦታዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት የምግብ እርዳታ ማድረስ በጭራሽ የማይቻልባቸው እና በከፊል የሚቻልባቸው በርካታ ቦታዎችን በምስል አስደግፎ አቅርቧል።

በጭራሽ የእርዳታ አቅርቦት የማይቻልባቸው በሎ ከጠቀሳቸው ቦታዎች መካከል የጎጃም ዞኖች ይገኙበታል፤ ደጋ ዳሞት፣ ደቡብ መጫ፣ ደጋ ዳሞት፣ ጃዊ፣ ወንበርማ ተጠቅሰዋል።

በጎንደር መካነ እየሱስ፣ ታች ጋይንት፣ ዳውንት፣ መና መከታዋ የተጠቀሱ ሲሆን በወሎ መሃል ሳይንት ተጠቅሷል፤ በሸዋም መራቢቴ፣ ኤፍራታና ግድም፣ መንዝ ላሎ ምድር፣ ተካተዋል።

ማስተባበሪያው በስዕላዊ መግለጫ አስደግፎ ባወጣው መረጃ አብዘሃኛዎቹ የክልሉ አከባቢዎች በከፊል ተደራሽ ናቸው ብሏል።

በምስራቅ አማራ በተሻለ ሁኔታ መድረስ ችያለሁ ሲል የገለጸው ማስተባበሪያው በዚህም እጅግ አስፈላጊ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ማቅረቡን ጠቁሟል።

ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ወረዳ ላይ በተያዘው የመጋቢት ወር አስቸኳይ የነፍስ አድን እርዳታ መስጠት መቻሉን የጠቆመው ማስተባበሪያው ሁለት የጤና ማዕከላት ላይ የህክምና እርዳታ ማድረሱን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ማስተባበሪያው በክልሉ በበቂ ሁኔታ የእርዳታ አቅርቦት ማድረስ የሚችለው በጥቂት ወረዳዎች መሆኑን ጠቅሶ ከነዚህ አከባቢዎችም ዋግህምራ ዞን አንዱ መሆኑን ገልጿል፤ ደቡብ ወሎ ደሴ ዙሪያ እና የኦሮሞ ልዩ ዞን ውስጥ ደግሞ ኬሚሴ አከባቢ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ መቻሉን አስታውቋል።

አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ቦታዎች ብዙ መሆናቸውን የጠቆመው ማስተባበሪያው በተለይ ግን ዋግ ህምራ፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ናቸው ብሏል።

አንዳንድ ወረዳዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው አይደሉም በሚል ተመድበው የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ የወረዳዎቹ የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የተረጂ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ ነው ሲል አሳስቧል።

ከባለፈው አመት የተሻለ ምርት ቢሰበሰብም የምግብ እህሎች ዋጋ ግን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያስታወቀው መምሪያው የአቅርቦት እጥረትም አለ ብሏል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ መቆም በርካቶች የምግብ እርዳታ እንዳያገኙ ማድረጉንም አመላክቷል።

በተጨማሪም፣ የተገደበ የገንዘብ ድጋፍ፣ በቂ አጋር የሆኑ የረድኤት ድርጅቶች በክልሉ አለመገኘታቸው፣ የጸጥታ ችግር እና አሁንም የቀጠለው በመንግስት እና በታጣቂዎች መካከል በሚካሄዱ በመሳሪያ የተደረፉ ግጭቶች ምክንያት የክልሉ በርካታ አካባቢዎች ተደራሽ አለመሆናቸው ተደማምሮ ለተረጂዎች የሚሰጠው ምላሽ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አመላክቷል።

በክልሉ በረድኤት ሰራተኞች ላይ የሚፈጸመው ወንጀል መባባስ ሁኔታዎች አስቸጋሪ አድርጓቸዋል ብሏል፤ ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት ስምንት የረድኤት ሰራተኞች መገደላቸው እና 24 ሰዎች መታገታቸውን አውስቷል።

የክልሉ ሁሉም አከባቢዎች እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም አካላት እንዲተባበሩት ማስተባበሪያው ጠይቋል፤ በተያዘው የመጋቢት ወር ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች በተለይም ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም እና ሰሜን ወሎ ዞኖች እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን አስፈላጊ ድርድር አድርጊያለሁ ብሏል።

በተያዘው አመት ታህሰስ ወር ላይ “በጸጥታ ችግር”ለሁለት ወራት እርዳታ ባልደረሰበት ቡግና ወረዳ በሀገር ሽማግሌዎች ስምምነት መደረጉን ተከትሎ የእህል እርዳታ መጓጓዝ መጀመሩ የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

ስምምነቱን ተከትሎ ከታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ “በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር” በሆነችው በቡግና ወረዳ ከሁለት ወራት በኋላ ከ110 ሺሕ በላይ ለሆኑ ሰዎች ከ16 ሺሕ ኩንታል በላይ የርዳታ እህል ወደ ስፍራው እየተጓጓዘ እንደሚገኝ በወቅቱ በቀረበው ዘገባ ተመላክቷል፡፡

ባሳለፍነው የካቲት ወር ባቀረብ ነው ዘገባ በአማራ ክልል በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ከ250 ሺህ በላይ ሕጻናት ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማስታወቁን ማቅረባችን ይታወሳል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ሥርዓተ ምግብ የቅኝት እና ምላሽ ሰጭ ባለሙያ ኃይሌ አያሌው በክልል 43 ወረዳዎች በድርቅ መጎዳታቸውን ጠቅሰው፤ በወረዳዎቹ ከ9 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በድርቁ ምክንያት የዕለት ምግብ እና ውኃ ፍለጋ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንደወጡ መግለጻቸውም በዘገባው ተካቷል።

በአማራ ክልል ባለፈው የክረምት ወራት የሚጠበቀው ዝናብ ባለመጣሉ በተለይ በዋግ ኀምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ውስጥ የተከሰተው አስከፊ ድርቅ በእንስሳትና በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ነዋሪዎች መናገራቸውን የተመለከተ ዘገባም መቅረቡ ይታወሳል።

በሰሜን ጎንደር ዞን 6 ወረዳዎችና 83 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ 452 ሺህ ሰዎች ለእለት እርዳታ የተዳረጉ ሲሆን 104 ሺህ የሚሆኑት ህፃናት፣ 14 ሺህ እናቶችና ነብሰጡሮች መሆናቸውን ወረዳውን ዋቢ በማድረግ በዘገባው ተመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button