
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በህጻናት መቀንጨርና በምግብ እጥረት ለተጎዱ ከ110 ሺህ በላይ ሰዎች ከሁለት ወራት በኋላ የርዳታ እህል መጓጓዝ መጀመሩን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
እርዳታው መጓጓዝ የጀመረው በጸጥታ ችግር ምክንያት ላለፉት ሁለት ወራት እርዳታ መድረስ ባለመቻሉ በሀገር ሽማግሌዎች ስምምነት መደረጉን ተከትሎ መሆኑን የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ይመር ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
የጽሕፈት ቤት ኃላፊው “የቡግና እና ላስታ ዙርያ ወረዳዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተከሰተው ግጭት ምክንያት አስፈላጊውን እርዳታ በወቅቱ ማስገባት አልተቻለም” ብለዋል፡፡
በዚህም የቡግና ወረዳ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የግብርና እና የጤና ባለሙያዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በላሊበላ ከተማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው “እርዳታው ይምጣ እንጂ የማዳረሱን ሃላፊነት እኛ እንወስዳለን” በሚል ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ ከታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ “በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር” በሆነችው በቡግና ወረዳ ከሁለት ወራት በኋላ ከ110 ሺሕ በላይ ለሆኑ ሰዎች ከ16 ሺሕ ኩንታል በላይ የርዳታ እህል ወደ ስፍራው እየተጓጓዘ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በላሊበላ ከተማ 34ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች 5100 ኩንታል እርዳታ ለፌደራል መንግሥት መጠየቁን ጠቅሰው እስከዚህ ሰዓት ድረስ 1200 ኩንታል መግባቱን አመላክተዋል፡፡
ከቡግና ወረዳ በተጨማሪ የምግብ እጥረቱ በተከሰተበት ሌሎች ወረዳዎች የጸጥታ ችግር ባለመኖሩ የእርዳታ እህሎች እንዲሁም አልሚ ምግቦችና መድሃኒቶች በወቅቱ ተጓጉዘው እንዲያገግሙ ተደርገዋል ብለዋል፡፡
አቶ አለሙ ይመር አከባቢው በህጻናት መቀንጨር እና በምግብ እጥረት ችግር በተደጋጋሚ እንደሚጠቃና በአከባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ሁኔታውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ቀውስ የሚገልጹ ሪፖርቶችን እየተከታተለ መሆኑን ትናንት ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
“የኢትዮጵያ ህዝብን ለመደገፍ አጋሮቻችን ምግብ እና አልሚ ምግቦችን ወደተጠቁት ስፍራዎች እየላኩ ነው” ያለው ኤምባሲው ሁኔታውን በቀጣይም በመከታተል ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተከሰተ ድርቅ እና የምግብ እጥረት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ጨምሮ 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መጎዳታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በወቅቱ የቡግና ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ዓለሙ እንደገለጹት በአማራ ክልል የተነሳው ግጭት አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያለፈው ሲሆን ከግጭቱ ባለፈ ወረዳው “ዝናብ አጠር እና በተፈጥሮ የተጎዳ” በመሆኑ እንዲሁም በሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት የምግብ እጥረት መከሰቱን አስታውቀዋል።
አክለውም “ለጋሽ ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደ ወረዳው ገብተው ማገዝ ካልቻሉ የሰው ሕይወት እንደሚያልፍ ግልጽ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።አስ