ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ ክፍፍል እና አለመግባባት ውስጥ የሚገኘው ህወሓት ከምርጫ ቦርድ የተጋባው እሰጣ ገባ የትግራይን ሰላም አደጋ ላይ ይጥለው ይሆን?

በሚሊዮን በየነ  @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16/ 2017 ዓ/ም፦ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለበርካታ አስርት ዓመታት የምስረታውን ቀን በታላቅ ዝግጅቶች ሲያከብር ቆይቷል። ይሁን እንጂ ባለፈው ወር የተከበረው የድርጅቱ 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከቀድሞው የተለየ ነበር። ይህም የሆነው ፓርቲው ውስጣዊ መከፋፈል እና ህጋዊ ሰውነቱን መልሶ ለማግኘት እያደረገ ያለውን ትግል ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየሉ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ በማክበሩ ነው።

ህወሓት ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ለ11 ቀናት ሳካሂደው የነበረውን የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ስብሰባ እና ግምገማ ማጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “በ50 አመታት ታሪኬ አጋጥሞኝ የማያውቅ ፈተና ውስጥ ነኝ” ሲል አስታውቋል።

የትግራይ ህዝብ ወደ ሰላም እንዲሸጋገር ያደረገ ወሳኝ እርምጃ ነው ያለውን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአመራር ክፍተት ሳቢያ ሙሉ ለሙሉ እንዳይተገበር ማድረጉን ጠቅሷል። የፓርቲው ኃላፊዎችም የህወሓት ውስጣዊ አለመግባባት የስምምነቱን ተግባራዊነት ማዘግየቱ ተናግረዋል።

ፓርቲው በመግለጫው ተልዕኮውን ለመወጣት ማዕከላዊ ኮሚቴው ተግዳሮች እንዳጋጠመው በመግለጽ፤ “ቡድንተኝነት፣ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት፣ ጎጠኝነት እና ሙስና ዋነኛ ችግሮች” መሆናቸውን ገልጿል።

ይህን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በሚመራ ቡድን መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተፈጠረ። ይህ መከፋፈል የደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበሩ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ነባር አባላቱን እና ከፍተኛ አመራሮቹን በ14ኛው ጉባዔ እንዲያግድ አድርጓል። 

ይህንንም ተከትሎ የደብረጽዮን አመራር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸውን ጨምሮ አምስት አባላትን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነት ማንሳቱን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በምላሹም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የደበረጽዮን ቡድን “መፈንቅለ መንግስት” ድርጊት ክልሉን “እንዳይረጋጋ” ለማድረግ ሙከራ አድርጓል ሲል ከሷል። ከሁለት ወራትም በፊት የትግራይ ሃይሎች ከፍተኛ አመራሮች ጊዜያዊ አስተዳደሩን “የተዳከመ” እና “ኃላፊነቱን መወጣት አለመቻሉን” በመግለጽ ለመበተን እና እንደገና ለማዋቀር መወሰናቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል።

የትግራይ ኃይል አመራሮች በጥር ወር በሰጡት መግለጫ በጊዜያዊ አስተዳደሩ “ቁልፍ ሥልጣን የነበራቸው አመራር እና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት በመፈጸም የውጭ ኃይል መሣሪያ ሆነዋል” ብለዋል።

አንደኛውን የህወሓት ቡድን የሚመሩት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሁለት ሳምንታት በፊት አራት ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችን ‘ከመንግስት ውሳኔዎች ያፈነገጡ’ እና ‘ክልሉን ወደ ውስጣዊ ግጭት የሚጎትቱ’ ተግባራት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ከስራ ካገደ በኋላ በክልሉ ውጥረቶች ተባብሰዋል።

ይህን ተከትሎም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ ለመቆጣጠር ከፌደራል መንግስት ‘አስፈላጊውን ድጋፍ’ የጠየቀ ሲሆን፣ በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን ጥሪውን ውድቅ አድርጓል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) 03 መጋቢት 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የተደረገው ጥሪ ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አደጋ ነው ሲል አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሰጡት ማብራሪያ፤ ክልሉ ላይ “የህግ ተቀባይነት ያጡ እና ከጦርነት ትርፍ እናገኛለን የሚሉና በጥቅም የተሳሰሩ የተወሰኑ የህወሃት ቡድን” የተወሰኑ ከፍተኛ መኮንኖችን በመያዝ ክልሉን አደጋ ላይ እየከተቱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በማግስቱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የተመራ ውይይት በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር አካሄደዋል።

በመድረኩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፤ “ራሱን ነጥሎ የወጣው የህወሓት አንጃ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዳይተገበር እንቅፋት ሆኗል” ሲሉ ቡድኑን ከሰዋል። በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄድ የሰጠውን መመሪያ አለመቀበሉን አስረድተዋል።

ከተመሰረተ 50ኛ አመቱን በቅርቡ ያከበረው አንጋፋው የፖለቲካ ፓርቲ ህወሓት በትግራይ ተጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህጋዊ ሰውነት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ተከትሎ ከፌዴራል መንግስት ጋር አለመግባባትን አስከትሏል።

ይህም ውጥረት ተባብሶ በቅርቡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድርጅቱን ለሶስት ወር ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማገዱን እና ፍቃዱን የመሰረዝ ማስጠንቃቂያ መስጠቱን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአህጉረ አፍሪካ ሃምሳ አመታት እንደኔ እድሜ ያለው ፓርቲ የለም የሚለው ህወሓት በ50ኛ አመቱ ዋዜማ (ስድስት ቀናት ሲቀሩት) ከምርጫ ቦርድ በኩል የተላለፈበት እገዳና ማስጠንቀቂያ በመካከላቸው የተፈጠረው እሰጣገባን አባብሶታል።

የቦርዱ እና የህወሓት “እሰጣገባ” የጀመረው በጦርነቱ ውቅት በሽብርተኝነት ተፈርጆ የምዝገባ ፍቃዱ የተሰረዘው ህወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በምርጫ ቦርድ የነበረው ህጋዊ ሰውነት አለመመለሱን እና  በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ አንደሚንቀሳቀስ መደረጉን ተከትሎ ነው። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲያደርግም አሳስቦ ነበር።

በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር ) የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 5 እስከ ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ያደረገው ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “ ህወሓት የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የተናጠል ውሳኔ ዛሬ ይሁን ነገ አይቀበልም” ሲል ገልጿል።

ህወሓት “እኔ ህጋዊ ሰውነቴ ነው ሊመለስልኝ የሚገባው ምክንያቱም ደግሞ የሁለት አመቱን የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ፈራሚ ነኝ  ሲል” መልስ ሰጥቷል። ህወሓት የቦርዱን ውሳኔ “ምንም ህጋዊ ተርጉም የሌለው” ሲል በመተቸት ቦርዱ የሄደበት ርቀት “ያሳዝናል” ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 6 ባወጣው መግለጫ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ጠቅላላ ጉባዔ ማድረን ጨምሮ “በህግ የተጣለበትን ግዴታዎች ባለመወጣቱ” ለሶስት ወራት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አግዷል። ቦርዱ ፓርቲው በሦስት ወራት የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር የፓርቲው ምዝገባ እንደሚሰረዝ ገልጿል።

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ አማኑኤል አሰፋ “ምርጫ ቦርድ ያልጠየቅነውን በመስጠት ያልተቀበልነውን እንደተቀበልነው በማድረግ ሊዳኘን እየሞከረ ነው፣ የዲሞክራሲ ተቋም ሆኖ እያለ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ለማቀጨጭ እየተንቀሳቀሰ እና እየገፋን ነው” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

የፕሪቶርያው ስምምነት ከተፈረመ ከወራት በኋላ “የተሰረዘ ህጋዊ ሰውነታችን ይሰጠን ብለን ጠይቀናል” ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ምርጫ ቦርድ “የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ህግ የለኝም” ሲል ምላሽ እንደሰጣቸው አሰታውሰዋል። “ከዛም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ንግግር አድርገን፤ ምርጫ ቦርድ ህግ የለኝም የሚል ከሆነ የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነት መመለስ የሚያስችል ህግ እናወጣለን ብለውናል” ሲሉ ገልጸዋል።

“ከዚያ ህግ አወጡና በልዩ ሁኔታ መዝግበናችኋል አሉን” ብለዋል።

ፓርቲው በልዩ ሁኔታ በቦርዱ ተመዝግቦ “የምዝገባ ሰርተፍኬት ተቀብሏል፣ ከዚያ ግን ውሳኔውን አልቀበልም ሲል በአደባባይ ይገልጻል” የሚል ትችቶች ይቀርቡበታል፤ ከነዚህም መካከል የባይቶና ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሩ ጸጋዘአብ (ዶ/ር) ይገኙበታል።

ፓርቲው “ተስማምቶ ከቦርዱ ዕውቅና ወስዷል” ያሉት ዶ/ር ጸጋዘአብ ወይ ከመጀመሪያው መቀበል አልነበረባቸው እንጂ ከተቀበሉ በኋላ ህግ አለማክበር “ማናለብኝነት ነው” ሲሉ ተችተዋል።

ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ አንቀበልም ብሎ የጻፈው ደብዳቤ የለም ያሉት ጸጋዘአብ፤ “መታወቅ ያለበት ጉዳይ መግለጫ እና ደብዳቤ ይለያያል፤ ማንም ስለ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ማውጣት ይችላል፣ አስተያየት ትችትል ማቅረብ ይቻላል። ምርጫ ቦርድ አሰራሩን እየተከተለ በይፋ ደብዳቤ ሲጽፍ እንደተመለከትነው ሁሉ ፓርቲውም በይፋ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ነበር መጻፍ የነበረበት፤ ይሄን ከፓርቲው አላየንም። የማይቀበሉት ከሆነ ምስክር ወረቀቱን መመለስ ነበረባቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

በዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ፤ ፓርቲው ግልጽ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ ብቻ ሳይሆን ለጠ/ሚኒስትር አብይም ጭምር መጻፉን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

“አዎ ውሳኔውን አልተቀበልነውም፣ የጠየቅነው ሌላ የሰጣችሁን ሌላ ብለን ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለምርጫ ቦርድ ልከናል” ብለዋል።

“ተቀብለውታል ማለት ዝም ብሎ የመስጠትና የመቀበል ተደርጎ መቆጠር የለበትም” ሲሉ ጠቁመው “ሰርተፊኬቱ እጅህ ላይ ከደረሰ ቴክኒካል ነው የሚሆነው፤ ፖለቲካሊ፣ ህጋዊ ተቀበልከው የሚባለው በተሰጠው ውሳኔ  የምርጫ ቦርድ እንዲቆጣጠርን እንዲዳኘን ስንፈቅድ ነው ፖለቲካሊ ተቀበልነው፣ በህግ ተቀበልነው የሚባለው” ብለዋል። በተጨማሪም “ህወሓት ሰርተፊኬቱን አይቶ ነው መወሰን ያለበት” ሲሉ ገልጸዋል።

የምርጫ ቦርድ እና ህወሓት እሰጣገባ ተጽዕኖ

አቶ አማኑኤል ምርጫ ቦርድ “ከህግ አልፎ የፖለቲካ ሴራ ውስጥ እየገባ ስለሆነ ተቋሙ ለዚህም ነው መግለጫ የሚያወጣው ሲሉ” ተችተዋል።

“ቦርዱ በትግራይ ክልል የፖለቲካ ጨዋታ እየተጫወተ ነው” ሲሉ የወቀሱት አማኑኤል “በክልሉ የፖለቲካ ሙቀቱ ቀዝቃዛ ሲል እሳት የመጨመር ሃላፊነት ነው፤ እየተጫወተ ያለው፣ ነዳጅ የመጨመር አይነት ሃላፊነት ነው እየተጫወቱ ያሉት” ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

ህወሓት ሊሰረዝ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ይህም “በፕሪቶርያው ስምምነት ላይ አደጋ አለው” የሚሉ ስጋቶች ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የህግ ሙሁሩ እና በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብት ተመራማሪው ታደለ ገ/መድህን “አዎ ችግር ይፈጥራል” ሲሉ ይሞግታሉ። የባይቶናው ጸጋዘአብ ደግሞ “ምንም ችግር አይፈጥርም” ባይ ናቸው።

ታደለ የፕሪቶርያው ስምምነት ባለቤት አልባ ይሆናል ችግሩም በዚያ አያቆምም ሀገርና አከባቢውን ይጎዳል ባይ ናቸው። ሀወሓት “እጁን አጣጠፎ አይቀመጥም” 50 አመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ እና እድሜ ጠገብ መሆኑን እና የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አስታውሰው “አጋር ፍለጋ መንቀሳቀሱ የማይቀር ነው እና የትግል ስልቱም ይቀየራል” ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተውናል።

ምርጫ ቦርድ ህወሓትን “ከመግፋት ይልቅ የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል” ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል፤ “አሁን እኮ ትግራይ ከኢትዮጰያ ጋር በመሬት ተጠበቀች እንጂ በህገመንግስት ቋንቋ አባል ነች ማለት አትችልም፤ ብቸኛ ድልድዩ የፕሪቶርያ ስምምነት ነው” ሲሉ ገልጸዋል። የፕሪቶርያው ስምምነት ፈራሚ ደግሞ ህወሓት ነው ሲሉ ጠቅሰው “ፓርቲው ህልውናው አከተመ ማለት ባለቤቱ ማን ሊሆን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

አቶ አማኑኤል ምረጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ተቋም ነውና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ህጋዊ የሆነ ትግል እንዲያካሄዱ ረጅም ርቀት ተጉዞ ማበረታታት፣ መስራት ሲገባው፤ “የፕሪቶሪያ ስምምነት ያክል ስምምነት የፈረመ ድርጅት ተገፍቶ እንዲወጣ፣ አማራጭ እንዲያጣ፤ የሰላማዊ፣ የፖለቲካዊ መንገዱ እንዲዘጋበት፤ ለኢትዮጵያ፤ ለሰላም በማይጠቅም መልኩ መንቀሳቀሱ በጣም ያሳዝናል፤ ለሀገሪቱ ምን እየሰራ ነው ያለው ይሄ ተቋም” ሲሉም ወቅሰዋል።

የህወሓት ጉዳይ በተለይም ከህጋዊ እንቅስቃሴው ጋር በተያያዘ ሆነ ወይም ከፌዴራል መንገስት ጋር ያለው ግኑኝነት በሚመለከት “ብቸኛው ህግ የፕሪቶርያ ስምምነት ነው” ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ የፕሪቶርያው ስምምነት ህወሓትን እና የፌደራል መንግስትን የሚያገናኝ ብቻ ሳይሆን ትግራይንና ፌዴሬሽኑ የፌደራል መንግቱ የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብለዋል።

የባይቶናው ጸጋዘአብ በዚህ ሀሳብ አይሰማሙም የቦርዱ ውሳኔ ለፕሪቶርያው ስምምነት የሚኖረው “ተጽእኖ የተጋነነ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

“ስምምነቱ በህወሓት ስም ስለተፈረመ ህወሓት ከሌለ ስምምነቱ አይኖርም የሚለው ሀሳብ አያስኬድም፤ የፕሪቶርያው ስምምነትን ከህወሓት ህልውና ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም” ያሉት የባይቶናው ጸጋዘአብ የፕሪቶርያው ስምምነት የትግራይ ህዝብ ስምምነት ነው፣ የሌላው ቢቀር ፓርቲው ባይቀጥል እንኳ የፕሪቶርያው ስምምነት መቀጠሉ የማይቀር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

“ለፖለቲካ ጨዋታ ሲባል የፕሪቶርያ ስምምነትን ከፓርቲው ህልውና ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም፤ የፕሪቶርያው ስምምነት የትግራይ ህዝብ ስምምነት ነው” ብለዋል።

ከነሃሴ 3 ቀን 2017 የምርጫ ቦርደ ውሳኔ በኋላ ውሳኔውን እንደማተቀበሉት አስታውቃችሁ ለምን ውዝግቡ ቀጠለ ስንል የጠየቅናቸው አቶ አማኑኤል ምርጫ ቦርድን ተጠያቂ አድርገዋል። ቦርዱ ለየትኛውም ፓርቲ አድርጎት አያውቅም ባሉት ሁኔታ በፓርቲያቸው ላይ ያወጣውን መግለጫ ብዛት በዋቢነት አስቀምጠዋል።

“ያልጠየቅነውን እንደሰጣችሁን አስባችሁ እኛን ለመቆጣጠርና ለመዳኘት አትሞክሩ፤ የፕሪቶርያውን ስምምነት መሰረት አድርጋችሁ መስራት ያለባችሁ ብለናቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰዎችህጉን ገንቢ በሆነ መልኩ መተርጎም አይፈልጉም” ሲሉ የወቀሱት አማኑኤል ተሻሽሎ ከወጣው አዋጅ ይልቅ 11/61 የሚባለው የቆየው የምርጫ አዋጅ፤ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የተሠረዘውን ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል የተሻለ እድል ነበረው ሲሉ ጠቁመዋል።

“በአዋጁ ላይ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲን ሊሰዝ ይችላል ይላል እንጂ የተሰረዘ ህጋዊ ሰውነት አይመለስም የሚል ነገር የለውም” ሲሉ አብራርተዋል። “ፓርቲው ወደ ስምምነት ከመጣ፣ ወደ ሰላም ከመጣ ፓርቲው ምን ይሆናል የሚል ነገር የለውም”፤ በህግ ቋንቋ ትርጉም ምን የሚባል ነገር አለ “ያልተከለከለ እንደተፈቀደ ይቆጠራል” የሚል ነገር አለ ሲሉ ጠቁመዋል።

“የምርጫ ቦርድ በትግራይ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ በመግባት ዲስትራክቲቭ ሮል እየተጫወተ ነው” ሲሉ የወነጀሉት አቶ አማኑኤል የቦርዱ መግለጫዎች እና አካሄዶቹ፤ “ህወሓት ሁለት ነው፣ ህወሓት ጉባኤ አላካሄደም፣ የህወሓት ጉባኤ ህጋዊ አይደለም በሚል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማገዝ ነው” ሲሉ ይኮንናሉ።

ይህ አይነት እንቅስቃሴዎች ለሚያደርጉ አካላት እና ግለሰቦች “ለጊዜውም ቢሆን ጉልበት የሚመስል ነገር እንዲያገኙ፣ የህግ ሽፋን ያለው እንዲመስል ነው እየጣረ ያለው” ብለዋል።

ሌላኛው ደግሞ በክልሉ “አጀንዳ እንዲፈጠር እየጣረ ነው” ሲሉ ተችተዋል። መግለጫ የሚያወጣባቸው ወቅቶችን በማመላከት፤ በተለይም በ50ኛ አመቱን እያከበረ በነበረበት ወቅት የወጣወን መግለጫ አሰታውሰው።

ታደለ ገ/መድህን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ላይ የሚያሳልፋቸው ወሳኔዎቸ በተለይም ከሰላም ስምምነት በኋላ በተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የህወሓት ሚናን ከግምት ውስጥ በማስገባት በክልሉ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተውናል።

 የህወሓት ቀጣይ ጉዞውን እንዴት ለማድረግ አስቧል?

ምክትል ሊቀመንበሩ፤ “እኛን ከፌደራል መንግስቱ ጋር የሚያስተሳስረን ገመድ፣ ፖለቲካዊ የሆነ ዶክመንት የፕሪቶርያ ስምምነት ነው፤ የፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት አድርገን ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እንቀሳቀሳለን” ብለዋል።

“አሁን ትግራይ በፌደራል መንግስቱ ወይም በፌዴራል ስርዓቱ ወይም ደግሞ በፌደሬሽኑ ምንም አይነት ውክልና የላትም፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የለችም፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የለችም፤ በስራ አስፈጻሚው፤ በሰራዊቱ በሁሉም የፌደራል መንግስቱ ተቋማት የለችም። ወደ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ለመመለስ ዋናው ድልድይ፣ ዋናው መሳሪያ የፕሪቶርያ ስምምነት ነው። የህወሃት ጉዳይ ትግራይ ውስጥ ካሉትን ትልልቅ ጉዳዮች አንዱ ነው” ሲሉ የፓርቲውን እንቅስቃሴ በፕሪቶርያው ስምምነት ብቻ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የህወሃት ቀጣይ እንቅስቃሴውን፣ ቀጣይ ጉዞውን በምን መልኩ ማድረግ አለበት? ብለን የጠየቅናቸው ታደለ ገ/መድህን ቅድሚያ ክፍፍሉን “ማስወገድ አልያም ማለዘብ” ይጠበቅበታል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። “የትግራይን ህዝብ ጥቅም በሚገባ የሚወክል አንድ ወጥ አቋም ለማሳየት ውስጣዊ ልዩነቶችን ማሸነፍ አለበት” ብለዋል።

ሌላኛው ደግሞ የህግ አማራጮችን መፈለግ መሆኑን ጠቁመው እገዳው “ኢ-ፍትሃዊ ነው” ተብሎ ከተገመተ በኢትዮጵያ ህግ ማዕቀፍ ውስጥ እርምጃዎች መወሰዱን በማረጋገጥ የህግ መንገዶችን መፈለግ ነው ይላሉ።

ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም “ይግባኝ ማለት ይገባዋል” ያሉት ታደለ ይህ እገዳ በሰላም ሂደት እና በክልሉ መረጋጋት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋዎች ማጉላት፣ ጉዳዩን ለመካለልና ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ መፈለግ ይጠቅመዋል ሲሉ ገልጸዋል።

እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ የትግራይ የፖለቲካ አካላት የህወሓትን የፖለቲካ ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ እና የክልሉ “ጥቅሞች” በሀገሪቱ ሰፊ የፖለቲካ ዲስኮርስ ውስጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ መወከላቸውን ለማረጋገጥ መስራት ይችላሉ።

ዶ/ር ፀጋዘአብ የባይቶና ለትግራይ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው “የፓርቲው በቦርዱ የተሰጠውን የቀጣይ ሶስት ወራት ግዜ ይጠቀምበታል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በመጨረሻም አቶ አማኑኤል ሁኔታውን “የፌደራል መንግስት በቀላሉ ሊያስተካክለው የሚችለው ነገር ነው” ሲሉ ገልጸው “ህግ ከሆነ ምርጫ ቦርድ የቸገረው የፌደራል መንግስት ህግ ማውጣት ይችላል፤ በዚህ መልኩ መፍታት እንችላለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው” ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button