
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም፡- ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ለመሾም ህዝቡ ጥቆማ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ተከትሎ ህወሓት የፌደራል መንግስት የፕሪቶርያ ስምምነትን “እየጣሰ ነው”፤ “የተናጠል” ውሳኔዎችን እያሳለፈ ይገኛል ሲል ትላንት መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ማታ ላይ ባወጣው መግለጫ ተቃወመ።
“ከሰላም መንገድ ላለመውጣት የሚቻለንን ሁሉ እንደምናደርግ ማረጋገጥ እንፈልጋለን” ብሏል።
በትግራይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያ ስምምነት ውጤት እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ብቸኛ ውሳኔ አይደለም ሲል የኮነነው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት የስምምነቱን መንፈስ እና ይዘት ወደ ጎን በመተው ተገቢ ባልሆኑ ህጎችን ብቻውን እየወሰነ ለመሄድ እየሰራ ይገኛል ብሏል።
ህወሓት በመግለጫው ተጥሰዋል ብሎ ከጠቀሳቸው ጉዳዮች መካከል ትላንት መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር አብይ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ለመሾም የጥቆማ ጥሪ ማቅረቡን የተመለከተው ይገኙበታል።
ሌላኛው “በስምምነቱ አንቀጽ 3 የተፈራረምነው አንዱ ተዋዋይ ወገን ሌላውን ወገን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያለማጥቃት ገዴታ አለበት የሚለውን እና ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እና ሚዲያ ስራዎች መከልከላቸውን ጠቅሶ መንግስት ጥሷቸዋል ብሏል።
እነዚህን ግልፅ ግዴታዎች በመጣስ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይን ህልውና የሚፈታኑ ሁኔታዎች እንዲፈጠር መስራት ከጀመረ ብዙ ግዜያትን አስቆጥሯል ሲል ገልጿል፤ ብዙ ሀብት በማፍሰስ እየተረባረበ ይገኛል ሲልም ኮንኗል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ መንግስት የሚተዳደሩ እንደ ነዳጅ የመሳሰሉ ሸቀጦች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ከልክሏል ሲል በመግለጫው የገለጸው ህወሓት በትግራይ የሚካሄዱ ህይወት አድን ስራዎች እንዲቆሙ በማድረግ በትግራይ ተወላጆች ህይዎት እና ኑሮ ላይ መጫወት/መቀለድ ቀጥሏል ሲል ተችቷል።
“የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ሰአት የተመረጠ መንግስት ሊኖረው በተገባ ነበር” ያለው የህወሓት መግለጫ “ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ በተከተለው የተሳሳተ አካሄድ የፖለቲካ መታመስ እንዲፈጠር በመስራቱ እውን ሊሆን አልቻለም” ሲል ገልጿል።
ህወሓት ከፌደራል መንግስት ጋር በቅርቡ መወያየቱን እና የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ለመቀየር መስማማቱን፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ ምትክ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ሀሳብ አቅርቦ መንግስትም ተቀብሎት ስምምነት ላይ መደረሱን በመግለጫው አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ስምምነቱን ወደጎን በመተው “በጠቅላይ ሚኒስትር የተላለፈው የፕሬዝዳንትነት ጥቆማ ጥሪ ፕሬዝዳንት የመሾም ስልጣን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናጠል ውሳኔ የሚያስመስል እና የፕሪቶርያ ስምምነትን የሚጥስ አካሄድ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ሲል ተችቷል።
በፌደራል መንግስት በኩል የክልሉን ህዝብ ሰላም የሚያምሱ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎችም እየተተገበሩ ናቸው ያለው መግለጫው የትግራይ ሰራዊት እና አመራሩ በኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት በ“በሬ ወለደ” እየተወነጀሉ ናቸው ሲል ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በግልጽ ከሚታዩ ህዝብን የሚጎዱ ሁከትና ከግጭት ከሚፈጥሩ ተግባሮቹ ተቆጥቦ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ጥቅምን በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እንዲያተኩር ጥሪ አቅርቧል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ለመሾም ህዝቡ በኢሜይል ጥቆማ እንዲሰጥ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በትግርኛ ባስተላለፉት መልዕክት መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወቃል።
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትን የመሾም ስልጣን በህግ ለጠ/ሚኒስትሩ የተሰጠ ቢሆንም ህዝቡን ማሳተፍ አስፈላጊ ሀኗል ሲሉ ገልጸዋል፤ በዚህም ህዝቡ በኢሜይል ጥቆማዎቹን ይላክ ሲሉ ጠይቀዋል።
“የትግራይ ህዝብ በተሟላ መንገድ በምርጫ መሪዎቹን እስኪመርጥ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አላማዎች በብቃት ይፈጽማሉ የምትሏቸውን፣ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ይችላሉ የምትሏቸውን እጩዎች በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኢሜይል ጥቆማችሁን ከመጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አድርሱኝ” ማለታቸውም በዘገባው ተካቷል። አስ