
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15/2017 ዓ.ም፡- የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህ የቀይ ባህር ወሰን የሌላቸው ሀገራት ተሳትፎን ‘እንደማይቀበሉ’ ገለጹ፤ በተጨማሪም ቀይ ባህርን መጠበቅ እና ማስተዳደር በዋናናት የባህሩ ድንበር ተጋሪ ሀገራት ተግባር እንዲሆን አሳስበዋል።
ሁለቱ ባለስልጣናት ይህንን የገለጹት ትላንት መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም በካይሮ በቀጠናዊ መረጋጋት ጉዳይ፣ ለሶማሊያ ድጋፍ በሚያደርጉበት መንገድ፣ ስለ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ እና ስለ ቀይባህር ደህንነት ዙሪያ በመከሩበት ወቅት መሆኑን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው አስታውቀዋል።
የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳላህ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተላከ መልዕክት ለግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ መስጠታቸውን የጠቆሙት ዘገባዎቹ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መልዕክት በሁለቱ ሀገራት ሁለትዮሽ ግንኙነት እና የጋራ በሆኑ አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ (ዶ/ር) እና የሀገሪቱ የደህንነት የደህንነት ሹም ሜጀር ጄነራል ሀሳን ራሽድ መገኘታቸውን ዘገባዎቹ አመላክተዋል።
የኦስማን ሳላህ እና አልሲሲ ውይይት በዋናነት ያተኮረው በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ነበር ሲሉ ቃል አቀባያቸው ሞሃመድ ኤልሸናዊ ገልጸዋል፤ ሶማሊያን ለማገዝ ሁለቱ ሀገራት ቁርጠኛ መሆናቸውም በውይይቱ ተገልጿል ብለዋል።
በሱዳን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ሁለቱም ባለስልጣናት መምከራቸውንም ቃል አቀባዩ ሞሃመድ ኤልሸናዊ አስታውቀዋል።
ቀይ ባህርን መጠበቅ እና ማስተዳደር በዋናናት የባህሩ ድንበር ተጋሪ ሀገራት ተግባር እንዲሆን አልሲሲ እና ሳላህ መክረዋል፤ የቀይ ባህር ወሰን የሌላቸው ሀገራት ተሳትፎን እንደማይቀበሉም ገልጸዋል ሲሉ የግብጽ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ መናገራቸውንም ዘገባዋቹ አካተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፤ ሰሞኑን “ከኤርትራ መንግስት ጋር ግጭት ይፈጠራል የሚል ስሞታዎች ይሰማል ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም” ማለታቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
አክለውም ኢትዮጵያ ያላት ፍላጎት “እንነጋገር ነው፤ ሰጥቶ መቀበል ባለበት፣ በገበያና ህዝቦችን በሚጠቅም መርህ ይህንን ችግር እልባት እናበጅለት፤ እንወያይ እንጂ እንዋጋ አላልንም” ሲሉ መደመጣቸውም በዘገባው ተካቷል።
የቀይ ባህር ፍላጎታችን ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከግብጽ፣ ከኬንያ የሚያጣላ፣ የሚያዋጋ መሆን የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁላችንም በቂ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ ባሳለፍነው ወር መገባደጃ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህ ወደ ርያድ በማቅናት የፕሬዝዳንት ኢሳያስን መልዕክት ለሳዖሲ አረብያ አልጋ ወራሽ ቢን ሳልማን ማድረሳቸውን የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ “በዲፕሎማሲ ወይም በወታደራዊ ኃይል” የባህር መዳረሻ እና የባህር ኃይል ቤዝ የማግኘት “የተሳሳተ እና ጊዜ ያለፈበት ምኞት” “ግራ አጋቢ ነው” ስትል ገልጻ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ “የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንድታከብር” ግፊት እንዲያደርግ ማሳቧን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን መቀበላቸውን ሲገልጹ ተስተካክሎ ነበር።
ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን አስከፊ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በሁለቱ ሃገራት መካከል ተሻሽሎ የነበረው ግንኙነት በድጋሚ ተቀዛቅዟል። አስ