
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር እና በሰሜን ጎጃም ዞን ከአርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች በተካሄዱ ውጊያዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በማዕከላዊ ጎንደር ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ በሁለቱ አካላት መካከል ግጭቶች ከአርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ማገርሸታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ “የፋኖ ታጣቂዎች” ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ ግጭቶች መካሄዳቸውን የገለጹት ነዋሪው አክለውም ታጣቂዎቹ የጎንደር ዙሪያ ጠዳ ክፍለከተማ አከባቢውን ተቆጣጥረው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
“የፋኖ ታጣቂዎች አርብ ዕለት ከምሽቱ 12 ሰዓት አከባቢ በጎንደር ጠዳ ክፍለከተማ ተኩስ ከፍተው ነበረ። ሲተኮስ ነው ያመሸው። ለሰዓታት ቆይተው ወጡ” ብለዋል።
በግጭቱ ምክንያት ከመንግሥት ጸጥታ አካላት እና ከፋኖ ታጣቂዎች በኩል በርካታ ተዋጊዎች እንደተገደሉ እንደሚያውቁ ገልጸው ሆኖም ይሄን ያህል ለማለት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
አክለውም በአሁኑ ሰዓት ግጭቶች መቀጠላቸውን ገልጸው ነዋሪው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደምበያ ወረዳ አይምባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው ስፍራው ከዚህ በፊት በ”ፋኖ ታጣቂዎች” ስር ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ሆኖም ከአርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደ አዲስ ባገረሸው ግጭት በትንሹ 3 ሰላማዊ ሰዎች በተባራሪ ጥይት ተመተው መገደላቸውን ጠቁመዋል።
አያይዘውም አሁን ላይ አይምባ ቀበሌን ጨምሮ ጎንደር ከተማ ዙርያ የሚገኙ በርካታ የገጠር ቀበሌዎች በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸውንና ውጊያዎች መቀጠላቸውን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ነዳጅ የጫኑ ሁለት ቦቲዎች ከጭልጋ ወደ ጎንደር ሲጓዙ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ መቃጠላቸውን አክለዋል።
አያይዘውም በምዕራብ በለሳ ወረዳ በተኩስ እሩምታ መሀል በትንሹ 5 ሰላማዊ ሰዎች ስለመገደላቸው ከቤተሰቦቻቸው መስማታቸውን አስረድተዋል።
ሌላኛው ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በክልሉ ሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት በከተማዋ የፋኖ ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ ውጊያዎች መቀስቀሳቸውን ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም ታጣቂዎቹ “ለምን ትምህርት ታስተምራላችሁ” በሚል 11 መምህራንን ሀሙስ መጋቢት 11ቀን 2017 ዓ.ም ከቤታቸው አስወጥተው መግደላቸውን ገልጸዋል።
“11 መምህራን ናቸው የተገደሉት። ከቤታቸው ወስደው ነው የፈጇቸው። ኮሎኔል ታደሠ ሙሉነህ እና ሽንብራ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚያስተምሩ ነበሩ” ብለዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን በይፋዊ የፌስቡክ ድረገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ “የዕውቀት አባት መምህራን ለምን አሥተማራችሁ ተብለው ተገድለዋል” ሲል አስታውቋል።
የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረሥላሴ ታዘብ ታጣቂ ኀይሎች ወደ ከተማዋ ሠርገው በመግባት አራት መምህራንን እና ከስምንት ዓመታት በፊት የመራዊ ከተማ ከንቲባ የነበሩ አሁን ላይ በሌላ ሙያ የነበሩን ግለሰብ ገድለዋል ብለዋል።
በተጨማሪም አንድ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አስተባባሪ የሆነ ግለሰብ በታጣቂዎች ታግቶ መወሰዱን ጠቁመዋል።
“አንደኛው መምህር ለማስተማር እየገባ ትምህርት ቤት በር ላይ ነው የገደሉት። ሌሎችን መምህራን እና የቀድሞውን ከንቲባ ደግሞ በየቤታቸው ሄደው ነው የገደሏቸው የታገተውን ግለሰብም ቤቱን ሰብረው ነው የወሰዱት” ብለዋል።
ግጭት በቀጠለበት የአማራ ክልል ከሰሞኑን የፋኖ ታጣቂዎች “ዘመቻ አንድነት” ሲሉ የጀመሩትን የተቀናጀ ዘመቻ ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች የሚካሄዱ ውጊያዎች እንደአዲስ አገርሽተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የፋኖ ታጣቂ ሀይሎች “ዘመቻ አንድነት” በሚል ስያሜ በተለያዩ የአማራ ክልል አከባቢዎች ያካሄዱትን የተቀናጀ ጥቃት በማክሸፍ ደምስሻለሁ ሲል መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መከላከያ በመግለጫው የፋኖ ታጣቂ ሀይሎች በክልሉ በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች ላይ ውድመት ፈጽሟል፣ የመንግስት መዋቅርን ለማፈራረስ ተንቀሳቅሷል ሲል ከሷል።
በተጨማሪም በዚህ ክልሉን ለማተራመስ እየተደረገ ባለው “ዘመቻ አንድነት” በተሰኘው እንቅስቃሴ ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ሀይለ ከጀርባ አሉበት ሲል ወንጅሏል።
የፋኖ ሀይሎች “ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷባቸዋል” ሲል መከላከያ ሰራዊቱ በመግለጫው አስታውቋል፤ “ተደምስሰዋል” ብሏል።
በዚህም በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ የሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ደምስሻለሁ ሲል አስታውቋል።
መከላከያ በመግለጫው በፋኖ ሀይሎች ላይ በሁለት ቀናት ብቻ 317 የተገደለ፣ 41 የተማረከ፣ 125 የቆሰለ፣ 27እጅ የሠጠ፣ 51 በምህረት የገባ፣ 15 መረጃ አቀባይ የተያዘ፣ በድምሩ 576 የሠው ኪሳራ አድርሻለሁ ብሏል።
ማረኳቸው ካላቸው መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶችም ውስጥም አንድ መትረየስን ጨምሮ “119 ክላሽ፣ 46 ኋላቀር መሣሪያ፣ 08 ሽጉጥ፣ 22 ቦምብ፣ 2290 የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ 28 ትጥቅ፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ተሽከርካሪ፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክል” ይገኙበታል።
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ አካላትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄዱ የሚገኙ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ለአብነትም በቅርቡ በክልሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን ነፍሴ ሳር ምድር ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ግጭት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገን ዘግበናል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ አዲገነት በተባለች ቀበሌ ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂውች መካከል በተካሄደ ግጭት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በክልሉ በተደጋጋሚ ግጭት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ምዕራብ ጎጃም ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በርካታ ንጹሃን ሰዎች ህይወት አልፏል።
ለአብነትም በዞኑ ጃቢ ጠህናን ወረዳ ጅማት እንቆቅማ ቀበሌ አርብ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከለ በተካሄደ “በከባድ መሳሪያ” በታገዘ ውጊያ የ14 ዓመት ታዳጊ እና መነኩሴን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም በክልሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ሸባ በተሰኘች ቀበሌ በእርሻ አውድማ ላይ የነበሩ 11 ሰዎች “በመንግሥት የጸጥታ አካላት” መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።አስ