ቢዝነስዜና

ዜና: “በሸቀጦች ላይ ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ፈቃድ እስከ መንጠቅ የሚያደርስ እርምጃ እወስዳለሁ” - የመቀለ ከተማ አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የመቀለ ከተማ አስተዳደር አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ባላቸው ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ሲል ገለጸ። አስተዳደሩ በሸቀጦች ላይ ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ፈቃድ እስከ መንጠቅ የሚያደርስ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።

በተጨማሪም እስከ መጋቢት 30 ድረስ ነዋሪው በተመጣጠነ ዋጋ ሸቀጦችን ሊገዛባቸው የሚችልባቸው የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን እንደሚያስጀምር ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ መሰረታዊ ሸቀጦች ግብይት ላይ ቁጥጥር እያደረገ ነው ሲሉ የገለጹት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካሳ ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን አምነው ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ እና ህገወጥ ንግድ ላይ” ቁጥጥር እየተደረገ ነው፤ የገበያ ማረጋጋት ላይ መሰረት አድርገን በትኩረት እየሰራን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“በቂ የሆነ የሸቀጥ አቅርቦት እያለ በጣት የሚቆጠሩ ነጋዴዎች በተለያዩ የከተማዋ ዳርቻዎች ሸቀጦችን እየከዘኑ እጥረት እየፈጠሩ ነው፤ አላግባብ ከፍተኛ ዋጋ እየጨመሩ ይገኛሉ” ያሉት ከንቲባው በነዚህ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየወሰድን ነው ብለዋል።

“በከተማዋ የሸቀጦች እጥረት የለም፣ ባደረግነው ዳሰሳ እና ከሚመለከታቸው አካላት በተለይም ከንግድ ቻምበር ጋር ባደረግነው ውይይት በቂ የሸቀጦች አቅርቦት አለ” ሲሉ አስታውቀዋል።

“ውስን፣ በጣት የሚቆጠሩ፣ መላ ነጋዴውን የማይወክሉ እና ስግብግብ” እያሉ ከንቲባው የጠሯቸው ነጋዴዎች እያደረሱት ያለውን መሰረታዊ ችግር ሁለት መሆናቸውን አይተናል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“አንደኛው የተወሰኑ ሸቀጦችን ከከተማዋ ዳርቻ በመሰወር ዋጋ እንዲወደድ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምንም አይነት ተጨማሪ እሴት ሳያደርጉ እና መሬት ላይ ዋጋ የሚያስጨምር ሁኔታ ሳይኖር ዋጋ ማናር፣ በእጥፍ መጨመር ናቸው” ብለዋል።

በዘሂህም ሳቢያ “እርምጃ ወደ መውሰድ ተገደናል” ሲሉ ገልጸዋል።

“በያዝነው ወር እስከ መጋቢት 30 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን እንመሰርታለን፣ ቦታዎችን የሚለይ ቡድን አቋቁመናል፤ ምግብ እና ምግብ ነክ በሆኑ እና የንጽህና መስጫ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፤ ለዚህ የሚያገለግሉ የገበያ ማዕከላት ይከፈታሉ” ብለዋል።

በመቀለ ከተማ በሚገኙ ክፍለ ከተማዋች በአስተዳደሩ እና የጸጥታ አካላት የተውጣጡ ቡድኖች ለሚያካሂዱት ቁጥጥር እና ዘመቻ ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

“በአንድ ሳምንት ብቻ ባካሄድነው ዘመቻ ከ17 ሺ ሊትር በላይ ነዳጅ የተደበቀ ተይዟል፣ መንግስት እንዲወርሰው ተደርጓል” ሲሉ ከንቲባው መናገራቸውን ከትግራይ ቴሌቪዢን እና ከድምጽ ወያነ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በትግራይ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ አንጻራዊ ሰላም ቢሰፍንም በክልሉ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ ህዝቡን ወደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እየዳረገው እንደሚገኝ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

የክልሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ከቅርብ ወራት ወዲህ በትግራይ የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ንሯል፣ የዕለት ፍጆታን ማሟላት አዳጋች ሁኗል።

ለዚህ በዋናነት የተጠቀሰው ምክንያት በክልሉ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲሆን በተለይም በክልሉ ገዢ ፓርቲ አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል እና የተካረረ ልዩነት ሁኔታውን እንዲባባስ ማድረጉን አመላክተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button