ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የምንዋጋው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ነው፤ የተመረጠን መንግሥትን በኃይል በማፍረስ ዘለን አራት ኪሎ ማለት ተራ ልምምድ  ሆኗል _ አብይ አህመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/ 2017 ዓ/ም፦ “በህዝብ የተመረጠን መንግሥት በሃይል በማፍረስ ዘለን አራት ኪሎ አራት ኪሎ ማለት ተራ ልምምድ  ሆኗል። ይህ በረሃ ላሉት ብቻ ሳይሆን በአንድ እግራቸው በርሀ በአንድ እግራቸው ደግሞ ፓርላማ ያሉትን ጭምር ይመለከታል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በፓርላማ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፤ “መንግስታችን ከኢህአዴግ ጋር አይወዳደርም። በአደረጃጀት፣ በእሳቤው በተግባሩም በማንኛውም መመዘኛ ብልጽግና ከኢህአዴግ ጋር አይወዳደርም” ብለዋል። 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጭያቄ ሀገሪቱ ያጋጠሟት ውስብስብ ችግሮች ፖለቲካ ወለድ ናቸው መፍትሔያቸውም ፖለቲካዊ እንጂ “የጠመንጃ አፈሙዝ ሊሆን አይገባም” ብለዋል።

ደሳለኝ “ኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ነበረ። ወደ ብልጽግና ያደረገው መለወጥ ደግሞ የሙሉ ጊዜ ጦረኛ እና ግጭት ጠማቂ አገዛዝ እንዲሆን አድርጎታል” ብልዋል። 

ባለፉት ስድስት ዓመታት በኦሮሚያ፣ አማራ እና አፋር ዛሬም ድረስ ደግሞ በኦሮሚያ እና አማራ “በቀጠለው ጦርነት ደሀው አርሶአደር እንደ ቅጠል እየረገፈ ነው” ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በትሪሊዮን የሚቆጠር ውድመት መድረሱን ጥናቶች ማመላከታቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታትና ከዛ በፊት ባሉ አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማራ በኦሮሚያ በአፋር በትግራይ በደቡብ በጋምቤላ እና በሌሎችም “ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በሰብአዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች፣ የጦር ወንጀሎች እንዲሁም የዘር ማጥፋቶች መፈጸማቸውን መንግስቶ እውቅና የማይሰጠውና ሃላፊነት የማይወስደው እንዲሁም ገለልተኛ አለምአቀፍ ጥናቶች እንዲካሄዱ የሚቀርቡ ጥሪዎችን የሚያጣጥለው ለምንድን ነው?” ሲሉም ጠ/ሚንስትሩን ጠይቀዋል።  

በድህነት አዙሪት ውስጥ የነበረች ሀገር ባለፉት ሰባት ዓመታት “የብልጽግናው አገዛዝ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ማባርያ ያጣ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አስገብቷታል” ሲሉም ከሰዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የዓለም ባንክ በ2022 “ኢትዮጵያ ዳሜጅ ኤንድ ኔድስ አሴስመንት” ብሎ ባወጣው ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የደረሰው ጉዳት ግምት 28 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል ሲል አክለዋል።

“የድሮን ጥቃት ዛሬም በአማራ ክልል ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሐን መገደላቸውን በዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ተዘግቧል” ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ያለመከሰስ መብት ያላቸው የምክርቤት አባላት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ ዶ/ር ካሣ ተሻገር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ተይዘው ለ20 ወራት ታስረው እንደሚገኙም አስረድተዋል።  

ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) “በጦር ሜዳ እያዋጉ ተይዘው የታሰሩ የህወሓት አመራሮችን በአጭር ግዜ የፈታ መንግሥት በገዢው ፓርቲ አሰራሮች ላይ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ አማራዎችን ይህን ያህል ያለ ፍርድ ማሰር የገዢው ፓርቲ ጥቅል ፓሊሲዎች በግላጭ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ብልጽግናን ወቅሰዋል። 

የሽግግር ፍትሕ ከመደረጉ በፊት የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲለዩ መደረግ አለበት ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ እንደሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደቶችን ሀገራዊ ችግሮችን እንዲፈቱ ከልብ የምንፈልግ ከሆነ በአማራ እና በኦሮሚያ እየተደረጉ ያሉ “አውዳሚ የወንድማማች ጦርነቶች” እንዲቆሙ መደረግ አለበት በማለት አሳስበዋል። 

የሰሜኑ ጦርነት እንዲቆም ያደረገው የፌደራል መንግስቱ ሲሆን አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ያሉ ጦርነቶች እንዲቆሙም “የሞራል እና የህግ ተጠያቂነት የሚወድቀው” በፌዴራል መንግስቱ ላይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ “በምርጫ ይሁንታ የተመረጠን መንግስት እጥላለሁ ሲሉ ዝም ማለት አይቻልም ተፈጥሮ እንደዛ አይደለም” ብለዋል።

“የምንዋጋው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ነው” ያሉት አብይ አህመድ  “ሥልጣን ላይ ያለው አካል ሃይል መጠቀም እንደሚችል የዓለምአቀፍ  ክፍት እውቀት ነው” ብለዋል።  

“በህዝብ የተመረጠን መናግሥት በሃይል በማፍረስ ዘለን አራት ኪሎ አራት ኪሎ ማለት ተራ ልምምድ ሆኗል። ይሄ በርሃ ላሉት ብቻ ሳይሆን በአንድ እግራቸው በርሀ በአንድ እግራቸው ደግሞ ፓርላማ ያሉትን ጭምር ይመለከታል” ሲል ተናግረዋል።

“የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ይህ ጦር ሰባቂ መንግስት ብለው ሲተቹ ህዝብ እንዳይወጣ እንዳይገባ ያደረገውን ኃይል ምነው አላየሁትም አልሰማሁትም አሉ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

አክለውም “በእርሶ ከተማ ቦምብ የሚያፈነዳውን፣ ሽማግሌ ላስታርቅ ብሎ ሲሄድ ከኢትዮጵያ ባህል ባፈነገጠ መልኩ በእምብሮክክ የመለሰውን ሃይል አላየሁትም ለምን አሉ?፤ ከሁሉም ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ በእርሶ እና በፓርቲዎ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የነበረውን የትግራይ ውጊያ አዝማች አልነበሩ እንዴ እርሶ? ትንሽ ሚዛን ቢጠብቁ ጠቃሚ ነበረ ብዬ አስባለሁ” ብለዋል። 

ጦርነትን በተመለከተ ወደኋላ መለስ ብለው የኢትዮጵያን የመቶ ዓመት ታሪክ ቢመለከቱ በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሰባት ዓመት ሙሉ ከአንድም ጎረቤት ጋር ያልተዋጋ “ብቸኛው መንግስት የእኛ መንግስት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። 

“ቤኒሻንጉል ላይ ኦሮሚያም በርካታ የታጣቂ ቡድን ክንፎች ወደ ሰላም ገብተዋል። በአማራ ክልልም ባለፉት 2 እና 3 ቀናት ብቻ ከ70 በላይ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ገብተዋል። መንግስታችን ከኢህአዴግ ጋር አይወዳደርም። በአደረጃጀት: በእሳቤው በተግባሩም በማንኛውም መመዘኛ ብልጽግና ከኢህአዴግ ጋር አይወዳደርም” በማለት ለአብኑ ተወካይ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  “በአማራም በኦሮሚያም ያሉ የጎበዝ አለቆች ይደራደራሉ። ሽማግሌ ይልካሉ። ይህን እዚህ ሳወራ እንትና ነው ልደራደር ያለው እያሉ እጅ ይቀስራሉ እንደዚህ የሚሉት ግን ራሳቸው ተደራዳሪዎች ናቸው። አምስት ስድስት አመት ቢዋጋ ማንም ሰው አራት ኪሎ ስለማይደርስ ዋጋ የለውም” ብለወል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button