
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/2017 ዓ.ም፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፤ ሰሞኑን “ከኤርትራ መንግስት ጋር ግጭት ይፈጠራል የሚል ስሞታዎች ይሰማል ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም” ብለዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ያላት ፍላጎት “እንነጋገር ነው፤ ሰጥቶ መቀበል ባለበት፣ በገበያና ህዝቦችን በሚጠቅም መርህ ይህንን ችግር እልባት እናበጅለት፤ እንወያይ እንጂ እንዋጋ አላልንም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የቀይ ባህር ፍላጎታችን ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከግብጽ፣ ከኬንያ የሚያጣላ፣ የሚያዋጋ መሆን የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁላችንም በቂ ነው ብለዋል።
አክለውም የኤርትራ ህዝብ “ወንድም ህዝብ ነው፤ ምስኪን ህዝብ ነው፤ እንደ ኢትዮጵያ ለማደግ የሚፈልግ ህዝብ ነው” ሲሉ ገልጸው፤ ተባብረን መልማት ተባብረን መስራት ነው እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ አቅድ አይደለም” ብለዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ላይ ማንም ሀገር ወረራ ሊፈጽም እና ከጀመርነው ህልም ሊያስቆመን ይችላል የሚል ስጋት የለብንም” ሲሉ ለህዝብ ተወካዮች ገልጸዋል። “ማንም ደፍሮ ሊሞክረን አይችለም በቂ ዝግጅት ስላለን፤ የምንዘጋጀው ግን ውጊያ ለማስቀረት ነው” ብለዋል።
ከሶማሊያ ጋር ይዋጋሉ የሚል ብዙ ስጋቶች እንደነበሩ ያስታወሱት አብይ፤ በንግግር መፈታቱን ገልጸው “እስከ ዛሬ ከማንም ጋር አንድ ጥይት ተቷክሰን አናውቅም ወደፊትም የእኛ ፍላጎት ይህ እንዲቀጥል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ” መሆኑን ያረጋገጡት ጠ/ሚንስትሩ “130 ሚሊዮን ህዝብ ጫፍ ጫፉ ተሰምሮለት፤ ተዘግቶ እስር ቤት ሊኖር አይችለም” ብለዋል። ማንኛውም ሰላም ወዳድ ነኝ የሚል የአለም መንግስት እና አካል በህግ አግባብ እና ንግድ መርህ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።
አብይ አህመድ ይህን ያሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳን ሙላቱ ተሾመ ኤርትራ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲዳከም በህወሓት ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር እየሰራች መሆኑን እና በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል ማሳሰባቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነው። በወቅቱ ኤርትራ የቀረበባትን ክስ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ የማነ በኩል ውድቅ አድርጋለች።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት “የማይቀር ይመስላል” “ወታደራዊ ዝግጅቶችም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ማለታቸውም ይታወሳል።
በተያዘው ሳምንት ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ “በዲፕሎማሲ ወይም በወታደራዊ ኃይል” የባህር መዳረሻ እና የባህር ኃይል ቤዝ የማግኘት “የተሳሳተ እና ጊዜ ያለፈበት ምኞት” “ግራ አጋቢ ነው” ስትል ገልጻ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ “የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንድታከብር” ግፊት እንዲያደርግ አሳስባለች።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ መቀመጫቸውን በሀገሪቱ ላደረጉ አምባሳደሮች፣ ለዲፕሎማቲክ ኮርፕስ አባላት እና ለተባበሩት መንግስትታት ድርጅት ተቋማት አመራሮች በአስመራ በሰጡት ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጅች ነው በሚል የሚቀርበው ወቀሳ “የሀሰት ክስ” ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኦስማን ሳልህ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ማብቃቱን ተከትሎ “በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ወዳለው የኤርትራ ድንበሮች መልሶ ተሰማርቷል” ብለዋል። አክለውም “ሰራዊቱ አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዳለ የሚናገር ወይም የሚያመለክት ማንኛውም አካል ይህንን የሚያደርገው ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ኤርትራን ማምለጫ ለማድረግ ነው” በማለት ገልጸዋል።
የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ጀምስ ሪሽ በትግራይ ክልል እና በአጎራባች አካባቢዎች ዳግም ግጭት ቢነሳ ‘አስከፊ’ አደጋ ያሰከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረትን በአስቸኳይ እንዲያረግቡም” ጠይቀዋል። አስ