
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15/ 2017 ዓ/ም፦ መንግስት በሀገሪቱ የነዳጅ እጥረት እና የጥቁር ገበያ ንግድ በተስፋፋበት ወቅት የቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ ላይ በሊትር እስከ አስራ አንድ ብር ጭማሪ አደረገ።
ከትላንት መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ጭማሪ ቤንዚን በሊትር 112 ብር ከ67 ሳንቲም መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ይህን የ11 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
እንዲሁም የናፍጣና ኬሮሲን ዋጋ በሊትር 107 ብር ከ93 ሳንቲም የደረሰ ሲሆን የዘጠኝ በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል።
ማስተካከያ በየሶስት ወሩ ከሚደረገው የነዳጅ ዋጋ ክለሳ አካል መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል። ይሁን እንጂ የአሁኑ ጭማሪ ከዚህ ቀደም ከተደረገው ማስተካከያ በሶስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተከሰተ ነው።
አዲስ ስታንዳርድ ታህስስ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የአንድ ሊትር የቤንዚን ዋጋ 100 ብርን ተሻግሮ 101.47 መድረሱንና የ11.5 በመቶ ጭማሪ መታየቱን መዘገቡ ይታወሳል።
የአሁኑ ጭማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፖርላማ ተገኝተው መንግስት የነዳጅ ዋጋን ለመደጎም እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ከፍተኛ ገንዘብ እየመደበ መሆኑን ከተናገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተደረገ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት የአለም አቀፉ የነዳጅ የገበያ ዋጋ በሊትር 129 ብር መድረሱን ገልጸው መንግስት በሊትር 28 ብር ድጎማ በመስጠት በአገር ውስጥ ነዳጅ በሊትር 101 ብር እንዲሸጥ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አክለውም መንግስት ቀደም ሲል ለነዳጅ ድጎማ 72 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን ተናግረው “ይህ ቢሆንም መንግስት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኙ ዜጎች ላይ ያለውን የገንዘብ ጫና ለመቀነስ በተለያዩ መሰረታዊ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ድጎማ መስጠቱን ቀጥሏል” ብለዋል።
ከፍተኛ ጭማሪ ካሳየው የነዳጅ ዋጋ ጎን ለጎን ሀገሪቱ ከባድ የነዳጅ እጥረት እያጋጠማት ይገኛል።
አዲስ ስታንዳርድ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ያለውን የነዳጅ እጥረት ሲዘግብ የቆየ ሲሆን ለአብነትም በቅርቡ በአፋር ክልል የባጃጅ አሽከርካሪዎች ለዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ቤንዚን ከማደያዎች ማግኘት አለመቻላቸውንና በዚህም ምክንያት በጥቁር ገበያ አንዱን ሊትር በ300 ብር ለመግዛት መገደዳቸውን ዘግበናል።
እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የሚገኙ አሽከርካሪዎችም እየተባባሰ የመጣውን የነዳጅ እጥረት የገለጹ ሲሆን፣ ይህም በጥቁር ገበያ የነዳጅ ሽያጭ መስፋፋት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።
በተጨማሪም በአማራ ክልል ያሉ አሽከርካሪዎች ከባድ የነዳጅ እጥረት እየተጋፈጡ መሆናቸውን ዘግበናል። ለአብነትም በባህር ዳር፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃን ባሉ ከተሞች ነዋሪዎች ሁኔታውን አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው፣ በጥቁር ገበያ የነዳጅ ዋጋ በሊትር 225 ብር መድረሱን ጠቁመዋል።
ችግሩ የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ወደሆነችው ሀዋሳም የተስፋፋ ሲሆን፣ አሽከርካሪዎች ከጥቁር ገበያ ሽያጭ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት እንደገጠማቸው ሪፖርት አድርገዋል።አስ