ህግ እና ፍትህዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ፍርዱ ቤቱ በፍቅር አጋሩ ግድያ በተጠረጠረው ድምጻዊ አንዱአለም ጎሳ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት17/ 2017 ዓ/ም፡- በፍቅር አጋሩ ቀነኒ አዱኛ ግድያ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘው ድምጻዊ አንዱአለም ጎሳ ዛሬ መጋቢት 17  ቀን 2017 ዓ/ም ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበ።

ተጠርጣሪው አንዱአለም ጎሳ ዛሬ ጠዋት አራዳ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት ከጠበቃው ጋር በቀረበበት ወቅት ፖሊስ በተሰጠው 13 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ ያሰባሰበውን ማስረጃ ለችሎቱ አቅርቧል።

ድምጻዊው የፍቅር አጋሩ በሆነችው ቀነኒ አዱኛ ግድያ ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ መጋቢት 4/ 2017 ዓ.ም አራዳ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት መቅረቡ ይታወሳል። ፖሊስ በዕለቱ በዋለው ችሎት ድምጻዊው ከሟች ጋር አብሮ የሚኖር በመሆኑ መጠርጠሩን ገልጿል። በዚህም መሰረት ፖሊስ ለምርመራ14 ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቆ 13 ቀን ተፈቅዶለት ለመጋቢት 17 ቀን 2017 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዛሬ በዋለው ችሎትም ፖሊስ በጉዳዪ ላይ 13 የሰው ምስክሮችን መሰብሰቡን ገልጾ ተጨማሪ መሰብሰብ ያለበት ማስረጃ ስላለ 14 የምርመራ ቀን እንዲጨመርለት ችሎቱን መጠየቁን የድምጻዊው ጠበቃ ሊበን አብዲ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

የተጠርጣሪው ጠበቃ እንደገለጹት፤ ፖልስ ባለፉት 13 የምርመራ ቀናት ውስጥ ያከናወነውን የሟች ቀነኒን አስክሬን ምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን በተደረገው የአስክሬን ምርመራም ከፍ ካለ ቦታ ላይ ወድቃ ህይወቷ ማለፉን ጠቁሟል። 

“ነገር ግን የአስከሬን ምርመራ ውጤትን በተመለከተ ከህክምና ባለሙያዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ስለጠየቅን እስኪደርሰን ተጨማሪ ቀናት ይሰጠን ብሎ ፖሊስ ጠይቋል” ሲሉ  ጠበቃው ተናግረዋል። 

በተጨማሪም በወደቀችበት በመኖሪያ ቤቷ ናሙና በመውሰድ ለፎረንሲክ ምርመራ ወደ ፌዴራል ፖሊስ መላኩን እና ውጤቱ እስካሁን አለመድረሱን አስረድቷል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዚህም መሰረት ፖሊስ  ቀረ ያለውን ምርመራ ለማጠናቀቅ 14 የምርመራ ቀን  እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የድምጻዊው ጠበቃ ሊበን አብዲ፤ እስከሚቀጥለው ችሎት ደንበኛቸው በዋስ እንዲለቀቁ ችሎቱን መጠየቃቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። “ቀነኒ ራሷን ከህንጻው ላይ ጥላ ነው። እሱ እንዳደረገ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም” ብለዋል።

“የምርመራው ውጤት ቢመጣው እሷ ከከፍታ ላይ መውደቋን እንጂ መገፍተሯን (መጣሏን) የማያሳይ በመሆኑ የዋስ መብቱ እንዲከበር ጠይቀናል” ያሉት ጠበቃው፤ “የምርመራ መዝገቡ በእሷ ሞት ላይ የእሱ እጅ እንደሌለበት የሚያሳይ ስለሆነ መዝገቡ እንዲታይለንም ጠይቀናል” ብለዋል። 

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ ጠበቃው የጠየቁትን የምርመራ መዝገብ ይዞ እንዲቀርብ እና የቀሩትን የምርመራ መረጃ እንዲያመጣ 12 ቀን መፍቀዱ ተገልጿል። 

የዋስትና ጥያቄውም የተጠቀሰው ማስረጃ በሚቀጥለው ችሎት ከቀረበ በኋላ ሰኞ መጋቢት 29  እንደሚታይ ፈርድ ቤቱ ገልጿል። 

ሞዴል እና የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ ከእጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ውዳሴ ከተሰኘው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ህይወቷ ማለፉን  በወቅቱ ፖሊስ አመልክቷል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button