
አዲስ አበባ፣ መጋቢት/ 10/2017 ዓ/ም፦ ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ “በዲፕሎማሲ ወይም በወታደራዊ ኃይል” የባህር መዳረሻ እና የባህር ኃይል ቤዝ የማግኘት “የተሳሳተ እና ጊዜ ያለፈበት ምኞት” “ግራ አጋቢ ነው” ስትል ገልጻ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ “የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንድታከብር” ግፊት እንዲያደርግ አሳሰበች።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ መቀመጫቸውን በሀገሪቱ ላደረጉ አምባሳደሮች፣ ለዲፕሎማቲክ ኮርፕስ አባላት እና ለተባበሩት መንግስትታት ድርጅት ተቋማት አመራሮች በአስመራ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው ይህ የተገለጸው። ማብራሪያውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ያጋሩት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል፤ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጅች ነው በሚል የሚቀርበው ወቀሳ “የሀሰት ክስ” ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኦስማን ሳልህ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ማብቃቱን ተከትሎ “በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ወዳለው የኤርትራ ድንበሮች መልሶ ተሰማርቷል” ብለዋል። አክለውም “ሰራዊቱ አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዳለ የሚናገር ወይም የሚያመለክት ማንኛውም አካል ይህንን የሚያደርገው ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ኤርትራን ማምለጫ ለማድረግ ነው” በማለት ገልጸዋል።
እነዚህን ክሶች የሚናገሩት “የቀድሞ የህወሓት አባላት” ናቸው ያሉት ኦስማን፤ “የኢትዮጵያ-ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ውድቅ ያደረጉ እና በኤርትራ የስርዓት ለውጥ እንዲደረግ የሰሩ ግን ያልተሳካላቸው” ናቸው ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተም ኦስማን፤ ኢርትራ “የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ” ነው የምትመለከተው እናም “ጣልቃ የመግባት ምንም ፍላጎት የላትም” ሲሉ ገልጸዋል። ኤርትራ በግዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሃት መካከል ባለው ግጭት ተሳትፋለች” በሚል የሚቀብ ክስ ካለ “ሙሉ ሉሙሉ ውድቅ ነው” ውድቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ ይህን የተናገሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳን ሙላቱ ተሾመ ኤርትራ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲዳከም በህወሓት ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር እየሰራች መሆኑን እና በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል ማሳሰባቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነው። በወቅቱ ኤርትራ የቀረበባትን ክስ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ የማነ በኩል ውድቅ አድርጋለች።
ባሳለፍነው ሳምንት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ትግራይ ውስጥ ከሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ ብዙ ወገኖች አሉ፤ የኤርትራ መንግሥት አንደኛው እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት “የማይቀር ይመስላል” “ወታደራዊ ዝግጅቶችም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ማለታቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ጀምስ ሪሽ በትግራይ ክልል እና በአጎራባች አካባቢዎች ዳግም ግጭት ቢነሳ ‘አስከፊ’ አደጋ ያሰከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረትን በአስቸኳይ እንዲያረግቡም” ጠይቀዋል። አስ