ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ ወደ ደብረማርቆስ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ አስቁመው ከ56 በላይ ሰዎች አግተው መወሰዳቸውን የአይን እማኞች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10/2017 ዓ.ም፡- ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ ወደ ደብረማርቆስ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ አስቁመው ከ56 በላይ ሰዎች አግተው  ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን የአይን እማኞች ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቁ።

ክስተቱ የተፈጠረው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ልዩ ስሙ አሊደሮ በተባለ ስፍራ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም መሆኑን ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የአይን እማኝ ገልፀዋል።

“ጥቃቱ የተፈጸመው አሊደሮ ነው፤ ከፊቼ እንደወጡ ከኢስት ፋብሪካ ዝቅ ብላ የምትገኝ ቦታ ናት” ያሉት እኚሁ የአይን እማኝ በወቅቱ እርሳቸው የከባድ ጭነት መኪና እያሽከረከሩ እንደነበረ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:30 ላይ መፈጸሙን የገለጹት እኚሁ የአይን እማኝ አክለውም የተኩስ እሩምታውን ተከትሎ የሚሄዱበትን አቅጣጫ ቀይረው የሚሆነውን ሲመለከቱ እንደነበረ አስታውሰዋል።

“ቅርብ ነበርን አውቶብሱ ጋር፤ ከኋላው ብዙም ሳንራራቅ እየተከታተልን ነበረ የምጓዘው። ከባድ ጭነት ጭነን ነበረ፤ ተኩስ ሲነሳ ባለንበት ቆምንና አዙረን ራቅ ካለ ቦታ ሆነን የሚሆነውን እንታዘብ ነበረ” ያሉት የአይን እማኙ አክለውም ተኩሱን ተከትሎ አውቶብሱ ለመቆም መገደዱን ገልጸዋል።

የተኩስ እሩምታውን ተከትሎ ታጣቂዎቹ ከኦሮሚያ ልዩ ሀይል ጋር ውጊያ መጀመራቸውን ገልጸው “በወቅቱ ታጣቂዎቹ በዛ ያለ ሐይል ነበራቸው፣ ግማሹ ከልዩ ሀይሉ ጋር ሲታኮስ ቀሪው ሀይል ተሳፋሪዎችን ከአውቶብስ እየደበደበ ያስወርድ ነበረ” ብለዋል።

አክለውም ሁኔታው እየከፋ መምጣቱን ሲመለከቱ አዙረው ወደ ፊቼ ከተማ መግባታቸውን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሌላኛው ለደህንነታቸው ሲሉ ስሜ ባይጠቀስ ያሉ አንድ ጥቃቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ የአይን እማኝ በበኩላቸው የነበረውን ሁኔታ “አስከፊ” ሲሉ ገልጸውታል።

በዚህ መስመር በተደጋጋሚ እንደሚጓዙ የሚገልጹት እኚሁ ግለሰብ ለስራ ጉዳይ ሚኒባሳቸውን እያሽከረከሩ በነበረበት ወቅት ከፊት ለፊታቸው ብዙም ባልራቀ ሁኔታ ሲሄድ በነበረ “ፈለገ ግዮን አውቶብስ” ላይ ተኩስ መከፈቱን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

“ቅልጥ ያለ ተኩስ ነበረ፤ ወዲያው አውቶብሱ ጎማው ላይ መትተውት ቆመ” ያሉት እኚሁ ግለሰብ “ተሳፋሪዎችን ክፉኛ እየደበደቡ ያስወርዷቸው ነበረ፤ ቦታው ዱር ገደል ነው። የት እንደሚወስዷቸው አላውቅም ብቻ እየደበደባቸው ወደ ታች ይወስዷቸው ነበረ” ብለዋል።

በተጨማሪም “ታጣቂዎቹ ጸጉረ ጉንጉን እና ሸኔ የሚባሉት ናቸው” ሲሉ ገልጸው ወዲያውም ከአከባቢው የጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት ወደኋላ የቀሩ ተሳፋሪዎች  በጥይት እሩምታው መካከል ምናልባትም ሳይጎዱ አይቀርም ብለዋል።

በአከባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚስተዋሉ የገለጹት እኚሁ ግለሰብ ባለው የደህንነት ስጋት የተነሳ ለስራ ጉዳይም ቢሆን በዚሁ መስመር የሚያደርጉትን ጉዞ ለመቀነስ መገደዳቸውን አክለዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ አዲስ ስታንዳርድ ጥቃቱ ደርሶበታል የተባለበት የፈለገ ግዮን አውቶብስ ጋር ደውሎ ያገኛቸው አንድ ሰራተኛ በበኩላቸው ጥቃቱ ከአዲስ አበባ ወደ ማርቆስ ሲጓዙ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በዚህም አንድ ሾፌር በጥይት መመታቱን እንደሰሙ ገልጸው ረዳቱን ጨምሮ በርካታ ተሳፋሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም አሁን ላይ ተሳፋሪዎቹ ያሉበትን ቦታ እንደማያውቁ ገልጸው “እኔ ይሄን ብቻ ነው የማውቀው” ሲሉ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከዚህ ቀደም ታጣቂዎች በአውቶብሶች ላይ የሚፈጽሟቸው እገታዎችን መዘገባችን ይታወሳል።

ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ከ160 በላይ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸውን ዋቢ አድርገን ዘግበናል።

በወቅቱ በደባርቅ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት የIT ተማሪ የሆነች ልጃቸው ከታገቱት መካከል እንደምትገኝ የገለፁ አንድ አባት “ከአጋቾቹ ጋር በየቀኑ እየተገናኘን ነው፣ አሁንም ገንዘቡን እንድንከፍል እየተጠየቅን ነው፣ልመናችንንም እየሰሙ አይደለም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፤ አክለውም አጋቾቹ ልጃቸውን ለመልቀቅ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ መሆኑን ተናግረዋል።

የታጋች አባት አክለውም ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም አፈናው በተፈጸመበት ወቅት ለባለሥልጣናት ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልፀው ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከመንግሥት የሰሙት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።

ሌላ ልጃቸው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ አመት ተማሪ የሆነች እና ከታገቱት ተማሪዎች መካከል የምትገኝ መሆኗን የተናገሩ አባትም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ሴት ልጃቸው እንዳልተፈታች እና ለማስለቀቂያ የሚሆን ገንዘብ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

አርሶ አደር የሆኑት አባት “ይህን ያህል ገንዘብ መያዝ ይቅርና ሰምቼም አላውቅም” በማለት ተናግረዋል። አክለውም ልጄን እንዲፈቱልኝ ከለመንኳቸው በኋላ በእግዚአብሔር እጅ ተውኩት” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው 3ኛ አመታዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ሪፖርቱ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ላይ የሚደርሰው አፈና እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል።

ከዚህ ቀደም አዲስ ስታንዳርድ በጥቅምት 2023 ባቀረበው ዘገባ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለገንዘብ ተብሎ የሚካሄደው አፈና እየጨመረ መምጣቱንና ለዚህም በመንግሥት ሃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የቀጠለው ግጭት መንሰኤ መሆኑን መገለጹ ያታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button