ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የመንግሥት ሠራተኞች ከጥቅምት ወር ጀምሮ ቃል የተገባላቸው የደመወዝ ጭማሪ እንዳልደረሳቸው ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2017 ዓ/ም፦ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪ ቃል የተገባላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ምንም አይነት ጭማሪ እንዳልደረሳቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ እና በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ ሁለት የመንግስት ሰራተኞች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ በመንግስት ቃል የተገባው ጭማሪ እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጸዋል።

ሰራተኞቹ “ከጥቅምት ወር ጀምሮ ያለውን ክፍያ ጨምሮ የደመወዝ ጭማሪው በዚህ በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚከፈል የሚጠቁሙ ወሬዎች በየቢሮአችን እየተናፈሱ ነው” ሲሉ ጠቅሰው ነገር ግን ይህን የሚገልጽ ምንም አይነት ይፋዊ ደብዳቤ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክ/ከ የሚሰሩ ሌላኛው ሠራተኛ በተመሳሳይ ሁኔታ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የደመወዝ ጭማሪ አለመደረጉን ገለጾ ነገር ግን በዚህ ወር ጭማሪው ይለቃቃል የሚል መረጃ እንዳለ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት አሻግሬ ቀለሙ (ስማቸው የተቀየረ)፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ወቅታዊ የደመወዝ ስኬል እና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ የስራ መደቦችን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ሰራተኞችን መረጃ ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል።

አክለውም “የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ የሲቪል ሰርቪሱ ደብዳቤ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን አውቃለሁ። ሆኖም እስካሁን ምንም አይነት ማረጋገጫ አልደረሰንም።” ብለዋል።

በዚህም የጣርማ በር ወረዳ ፋይናንስ ቢሮ የደመወዝ ማስተካከያ ደብዳቤዎችን ለማከፋፈል መዘግየቱን አቶ አሻግሬ አስረድተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“አሁን ላይ የ 10,150 ብር ደመወዝተኛ ነኝ  ጭማሪው ቢደረግልኝ 11,634 ብር ይደርሳል ወርሃዊ ደመወዜ ይሄም ቢሆን በተለይ የአምስት ዓመቷን ሴት ልጄን የትምህርት ቤት ወጪዋን ለመሸፈን የተወሰነ እፎይታ ያስገኝ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም መንግሥት የደመወዝ ማስተካከያ መደረጉን ባወጀ ማግስት እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ለአብነትም የምግብ ዋጋ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን እና የትራንስፖርት ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

አቶ አሻግሬ አክለውም መንግስት ቀደም ሲል የምግብ የዋጋ ግሽበትን ለመቅረፍ በአካባቢው ለሚገኙ የሸማቾች ማህበር ድጎማ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ቃል ሳይፈጸም መቅረቱን ገልጸው “በመንግሥት ሰራተኛው ባለው ከፍተኛ ፍላጎት ምክንያት በሸማቾች ማህበር ውስጥ የሚገኙት ሸቀጦች በፍጥነት ተሟጠው አልቀዋል። አቅርቦቱ በወረዳው ውስጥ ያሉትን በርካታ ሠራተኞች ለማገልገል በቂ አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።

ሆኖም እነዚህ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ አቶ አሻግሬ ቃል የተገባው የ900 ብር የደመወዝ ጭማሪ ለቤተሰባቸው የተወሰነ እፎይታ እንደሚሰጥ ተስፋ አድርገዋል።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በባሕር ዳር ከተማ ፋሲሎ ክፍለከተማ ሠራተኛ በበኩላቸው፤ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ አስቀድመው ከሚዲያ የሰሙ ቢሆንም ምንም አይነት ጭማሪውን የሚገልጽ ደብዳቤ ሆነ የተባለው የደመወዝ ጭማሪ እንዳልደረሳቸው አመላክተዋል። 

“ደመወዝ ይጨመራል መባሉን በሚዲያ ሲነገር ሰምቻለሁ። መስከረም ነበረ የጠበቅነው ከዛ ጥቅምት ላይ ይከፈላል የሚል ወሬ ሲናፈስ ነበር። እስከአሁን ግን የደረሰን ምንም ነገር የለም። እኔ አሁን እጄ ላይ 3600 ብር ነው በወር የሚደርሰኝ። እንደምታውቀው ካለው የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት አንፃር ፈጽሞ አይበቃህም።” ብለዋል።

ሌላኛዋ በዙሁ በፋሲሎ ክፍለከተማ በጽዳት ስራ የምተዳደር ግለሰብ በበኩሏ በወር የምታገኘው ደመወዝ አነስተኛ መሆኑ የኑሮዋን ፈተና መቋቋም እንዳትችል እንዳደረጋት ትገልጻለች።

“ጽዳት ነኝ እኔ። በዛ ነው ኑሮዬን የምገፋው። አንዲት ልጅ አለችኝ ገና ነፍስ ያላወቀች። በወር 1300 ብር ነው ገቢዬ። በጣም ከባድ ነው ኑሮ ብቻ ተመስገን እያልን ነው ጤና ስለሰጠን አማረነውም አይሆንም።” ያሉት እኚሁ ነዋሪ አያይዘውም የደመወዝ ጭማሪ ይደረጋል መባሉን ከሥራ ባልደረቦቻቸው መስማታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

“በእርግጥ እስከአሁን የተባለው ጭማሪ አልተደረገልንም። ብዙ ነው ሰው የሚያወራው ግማሹ ደግሞ በዚህ  በታህሳስ ወር ይገባል ይላል።” ያሉት ግለሰቧ አክለውም የተባለው ጭማሪ ቢደረግላቸው በትንሹም ቢሆን አንዳንድ ወጪዎቻቸውን ሊሸፍንላቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሰራተኞች በጥቅምት ወር አዲሱን የደመወዝ ጭማሪ ማግኘታቸውን ቢገልጽም፣ በርካታ የፌደራል መሥሪያ ቤት ሰራተኞች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች ግን ማስተካከያው እስካሁን እንዳልደረሳቸው መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር የደመወዝ ጭማሪውን ተግባራዊ ለማድረግ ያጋጠሙትን እንደ የተወሳሰቡ የመረጃ አሰባሰብ ጉዳዮች ያሉ ተግዳሮቶች አንስተው የፌደራል እና የክልል መንግስታት ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊነትን ጠቅሰዋል።

“ደመወዝን በሚመለከት ጭማሪ ለማድረግ ተስማምተናል።” ያሉት ጠ/ሚሩ ነገር ግን አፈፃፀሙ ከፌዴራል መንግስት ብቻ ሳይሆን ከክልል መንግስታትም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አጽንኦት ሰጥተዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፥ መንግስት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለሚካሄደው ማስተካከያ 91 ቢሊዮን ብር የመደበ ሲሆን: “ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች በትክክል ካልተተገበሩ ሀብቶች ያለአግባብ ሊውሉ ይችላሉ። ለውጡን ለማስፈጸም ግልጽነት ከሌለውም ለውጡ ራሱ ይከሽፋል።” ሲሉ አበክረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው ከአንድ ወር በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት “የደመወዝ ክፍያ ማስተካከያቸውን ያጠናቀቁ” የመንግስት ተቋማት አዲስ በፀደቀው የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ስኬል መሰረት ጭማሪውን አግኝተዋል።

በቀጣዮቹ ወራት የደመወዝ ጭማሪውኑ ለመሸፈንም የክልል መንግስታት በቂ ድጎማ እያገኙ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button