
አዲስ አበባ፣ ህዳር 2/2017 ዓ.ም፡- ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሰራተኞች በጥቅምት ወር አዲሱን የደመወዝ ጭማሪ ማግኘታቸውን ቢገልጽም፣ በርካታ የፌደራል መሥሪያ ቤት ሰራተኞች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች ግን ማስተካከያው እስካሁን እንዳልደረሳቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ መርማሪ የሆኑ ግለሰብ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት “የደመወዝ ማስተካከያው በጥቅምት ወር ይጀመራል ብለን ብንጠብቅም እስካሁን አልተከፈለንም” ብለዋል።
በተመሳሳይ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት በበኩላቸው እርሳቸውም ሆኑ ባልደረቦቻቸው ቃል የተገባውን ጭማሪ እንዳላገኙ አረጋግጠው ተግባራዊ ስለመሆኑ በይፋ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ያገኙት መረጃ አለመኖሩን ተናግረዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ሰራተኞችም የደሞዝ ጭማሪ እንዳልተደረገላቸው ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች መካከል በየካ፣ ቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች የሚሰሩ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ጭማሪው እንዳልደረሳቸው ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በቦሌ ክፍለ ከተማ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው “የደመወዝ ጭማሪው በዚህ ወር ተግባራዊ መደረግ ይጀመራል ብዬ አስቤ ይጠቅመኛል ብዬም ነበር። አሁን ግን መንግስት መቼ ተፈጻሚ እንደሚያደርገው እርግጠኛ አይደለሁም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በማህበራዊ ትስስር የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዳስታወቁት የገንዘብ ሚኒስቴር የተጨማሪ ክፍያ በጀቱን ለሚመለከታቸው ተቋማት መፍቀዱን ገልጸው፣ “በእኛ መስሪያ ቤትም በኩል የተስተካከለውን የጥቅምት ወር ደመወዝ ተከፍሏል” ብለዋል።
አክለውም “ሌሎችም እንደዚሁ የከፈሉ አሉ፤ የቀሩት ደግሞ የማጥራት ሥራ እየሰሩ ሊሆን ይችላል፤ እነዚያም ዝግጅታቸውን ሲያጠናቅቁ የተስተካከለው የጥቅምት ወር ክፍያ ታሳቢ በማድረግ የሚከፍሉ ይሆናል” ብለዋል።
“የተፈቀደው የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ ዘግይቷል፥ ቀርቷል የሚሉ ሃሳቦች እየተራመዱ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ አክለውም “በሲቪል ሰርቪስ በኩል የሚለቀቁ መረጃዎች ኦፊሴላዊና የሚተገበሩ መሆኑን መተማመን ጥሩ ነው” ብለዋል።
ከኮሚሽነሩ መግለጫ በተቃራኒ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግስት ሰራተኛ በበኩላቸው ጭማሪው እስካሁን እንዳልደረሳቸው በመግለጽ፣ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ ሕይወታችን “የማያቋርጥ ትግል ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሠራተኛ የሆኑት እኚህ ግለሰብ “የደመወዝ ጭማሪ ስንጠብቅ ነበር፤ ነገር ግን እንደገና መዘግየቱን ተረድተናል” ብለዋል።
የሶስት ልጆች አባት የሆኑት እኚሁ ግለሰብ የደመወዝ ማስተካከያ እንዳልተደረገላቸው ገልጸው: “የደመወዝ ማስተካከያ በተመለከተ ምንም አይነት ይፋዊ ደብዳቤ አልተሰጠንም” ብለዋል።
“ወርሃዊ ደሞዜ 6,000 ብር ነው፤ የኑሮ ውድነቱ ተባብሶ ቀጥሏል፤ አሁን ያለኝ ደሞዝ ቤተሰቤን ለማስተዳደር የሚበቃኝ አይደለም። ሕይወት ፈተና ሆናለች፣ እና ስለእሱ ማሰብ እንኳን በጣም ከባድ ነው” ሲሉ ምሬታቸውን አጋርተውናል።
አክለውም አሁን እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት የደመወዝ ማስተካከያውን በፍጥነት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
“ኑሮ አሻቅቧል። ቤተሰብ ስታስተዳድር ብዙ ወጪዎች ይኖሩብሃል። ልጆች ማስተማር አለ። አስበው እስኪ በቀን ውስጥ ለእራስህ ለመመገብ እስክትፈራ ድረስ ነው። ቁርስ በልተህ ምሣ ላትበላ ትችላለህ ምክንያቱም የምታስበው የምታስተዳድረውን ቤተሰብ ነው ለእነሱ ገንዘብ መቀነስ የለብህም።” ብለዋል።
አክለውም “ኑሮ እየናረ ሄደ። አሁን ያለው ብዙ ነገር ወደታች ይጎትትሃል።”ብለዋል።
በአንድ የመንግስት ተቋም ውስጥ የግራፊክስ ባለሞያ ሆነው ተቀጥረው የሚሰሩት እና የ10,000 ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሌላኛው የመንግስት ሰራተኛ በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት ይፋ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ መዘግየቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
“ምንም የገባልን ነገር የለም። የታቀደው ጭማሪ አሁን ካለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጋር አይሄድም።” ያሉት እኚሁ ግለሰብ አክለውም የደመወዝ ማስተካከያው ቢደረግ እንኳን በመንግስት ገቢ መኖር እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
“ኑሮ ውድነቱ ከምናገኘው ደመወዝ በበለጠ ፍጥነት እያሻቀበ ነው። በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ስል ከጓደኛዬ በደባልነት ነው የምኖረው ፣ ግን ያም ቢሆን ፈታኝ ነው።” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ እስከ 300% ሊጨምር እንደሚችል ማስታወቃቸውን ተከትሎ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር የሚገልጹ ዘገባዎች ባሳለፍነው አመት በ2016 ዓ.ም ነሐሴ ወር መጀመሪያ መውጣታቸው ይታወሳል።
ይህ የደመወዝ ማስተካከያ ሀሳቡ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም መጨረሻ ላይ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ዝቅተኛ እና ቋሚ ገቢ ላላቸው ሰዎች የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ያለመ ነው።
ይሁን እንጂ ፕሮፖዛሉ ከአንድ ወር በላይ ዘግይቶ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ይሁንታ አግኝቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የደመወዝ ማስተካከያው ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ እንደሚከፈል አስታውቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር የደመወዝ ጭማሪውን ተግባራዊ ለማድረግ ያጋጠሙትን እንደ የተወሳሰቡ የመረጃ አሰባሰብ ጉዳዮች ያሉ ተግዳሮቶች አንስተው የፌደራል እና የክልል መንግስታት ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊነትን ጠቅሰዋል።
“ደመወዝን በሚመለከት ጭማሪ ለማድረግ ተስማምተናል።” ያሉት ጠ/ሚሩ ነገር ግን አፈፃፀሙ ከፌዴራል መንግስት ብቻ ሳይሆን ከክልል መንግስታትም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፥ መንግስት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለሚካሄደው ማስተካከያ 91 ቢሊዮን ብር የመደበ ሲሆን: “ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች በትክክል ካልተተገበሩ ሀብቶች ያለአግባብ ሊውሉ ይችላሉ። ለውጡን ለማስፈጸም ግልጽነት ከሌለውም ለውጡ ራሱ ይከሽፋል።” ሲሉ አበክረዋል። አስ