
አዲስ አበባ፣ ህዳር 02/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደርቤ በለጠ በታጣቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
የአቶ ደርቤ በለጠ ታላቅ ወንድም የሆኑት አቶ ሲሳይ በለጠ የወንድማቸውን ግድያ አረጋግጠው አቶ ደርቤ በለጠ የ4 ልጆች አባት እንደነበሩ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስሜ ባይጠቀስ ያሉ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት የቆቦ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደርቤ በለጠ ትናንት ህዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት አከባቢ ቆቦ ከተማ በሚገኘው ሚኪኤሌ ሰለሞን ሆቴል ቁርስ እየተመገቡ ባለበት ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪው የጥቃቱ ፈጻሚዎች የ”ፋኖ” ታጣቂዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ ከእሳቸው በተጨማሪ የቆቦ ከተማ የመሬት ደስክ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የነበሩት ዶ/ር አዲሱ ወዳጆ እግራቸው አከባቢ በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም መቅደስ አለማየሁ የተባሉ ግለሰብ እና የሆስፒታል ዘበኛ የነበሩት አቶ አበበ ጫኔ በጥቃቱ ቆስለው ቆቦ ሆስፒታል መግባታቸውን አክለዋል።
እንዲሁም ከሌላ አከባቢ የመጣ እና የጥርስ መፋቂያ እያዞረ በመሸጥ ኑሮውን የሚገፋ አንድ ግለሰብ በአከባቢው በነበረበት ወቅት በተተኮሰበት ጥይት ክፉኛ ቆስሎ ወደ ወልዲያ ሪፈራል ሆስፒታል መላኩን አያይዘው ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በመንግስት ኃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመው አመራሮች ተገድለዋል።
የአቶ ደርቤ በለጠ ግድያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ላይ ካነጣጠሩት ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው።
ከዚህ ቀደም በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ሚሊሹ በቀለ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በተመሳሳይ መልኩ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በዞኑ የሚገኘው ኤፍራታ ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አልብስ አደፍራሽ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች መገደላቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ ሁለት የተለያዩ የመንግስት የፀጥታ ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡
በተመሳሳይ ምክትል ሳጅን ያለለት ደጉ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ባልታወቁ ግለሰቦች በጥይት ተደግለዋል፡፡
እንዲሁም የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት የስራ ባልደረባ የሆነችው ወ/ሪት ጽዮን ተገኝ እና የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ውብሸት አያሌው በተለያያ ጊዜ ማንነታቸው ባልታወቀ ግለሰቦች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ይታወሳል። አስ