
አዲስ አበባ፣ ህዳር 2/2017 ዓ.ም፡- በዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው እና በነሃሴ ወር ጉባኤ ያካሄደው የህወሓት ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ይፋዊ የመፈንቅለ መንግስት እያካሄደ ነው ሲል ትላንት ህዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
“ይህ ቡድን የመንግስት ስራዎችን ከማደናቀፍ አልፎ ይፋዊ የመፈንቅለ መንግስትን ወደ መፈፀምና ፍፁም ስርዓት አልበኝት ወደ ማስፋፋት ተሸጋግሯል” ብሏል።
“ህጋዊ ያልሆነ ጉባኤ ባካሄደው ቡድን በበላይነት የሚመራ የሚገራ ዘመቻ እየተካሄደብኝ ነው”፣ ስራየን በአግባቡ እንዳልሰራ እያደናቀፈብኝ ነው ሲል ኮንኗል።
“በመቐለ ከተማ፤ ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች የዚህ ተግባሩ ማረጋገጫ አብነቶች ናቸው” ሲልም ጠቁሟል።
“ህዝባችን ተስፋ እንዲቆርጥና በቀጣይ አዙሪት እንዲጠመድ ሆን ተብሎ የሚደረግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር እየተፈጸመ ነው” ሲል ተችቷል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው “ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ “ከትግራይ ሰራዊት አመራሮች ጋር ተረዳደተናል፤ ከላይ እስከ ታች የመንግስት መዋቅሩን ለመቆጣጠር ጨርሰናል” እያለ ሰፊ የማደናገር ተግባር ላይ ተጠምዷል ሲል አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ሀይማኖት አባቶች ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በሁለት ጎራ የተከፈሉትን የህወሓት አመራሮች በማቀራረብ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ህጎቻቸውን መሰረት አድርገው እንዲፈቱ እንዳስማሟቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ትላንት ህዳር 1 ቀን ባወጣው በመግለጫው ጉባኤወ ያካሄደው የነ ዶ/ር ደብረጺዮን ቡድን “በሰራዊት አመራሩም ሆነ በሃይማኖት አባቶች የተጀማመሩ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ሂደቶች ከልብ እንደማይቀበልም በአደባባይ እየገለፀ መጥቷል” ሲል ተችቷል።
ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሀት) ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋዊ የፌስቡክ ማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ በትግራይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች የተከናወነው መርሃግብር የማቀራረብ እንጂ “እርቅና ሽምግልና” አይደለም ሲል ገልጿል።
ልዩነቶችን በሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ በመርህ እና በስርዓት መፍታት ይገባል የሚለውን መርህ ላይ ያተኮረ አቋማችንን የሚያጠናክር በመሆኑ አባቶች የሰጡት ምክር እንደግፋለን ሲል ፓርቲው ባጋራው መረጃ አትቷል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር የሚገኘው የህወሓት ቡድን “ከማንኛውም አካል ጋርም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገርም ዝግጁ ናቸው” ያለው መግለጫው የሚደረገው ውይይት ግን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለማጥበብና ለመፍታት እንጂ የስልጣን ክፍፍል ለማድረግ አይደለምም፤ አይታሰብምም” ሲል አቋሙን አንጸባርቋል።
“መንግስታዊ ስልጣን ማን ይያዝ በሚል የስልጣን ክፍፍል ጉዳይ ላይ ግን በየትኛውም መመዘኛ ወደ ድርድር የማይቀርብ መሆኑን ግልፅ መሆን አለበት” ሲል ገልጿል።
በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል የትግራይን ሰላምና መልሶ የማገገም ሂደት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል ሲሉ የክልሉ ሙሁራን መግለጫቸውን የተመለከተ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል።
በአመራሩ መካከል የተፈጠሩት ውጥረቶች፤ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ በተከሰተው መፈናቀል እና ሰብአዊ ቀውስ ተጎጂ የሆነው የክልሉ ህዝብ ላይ ተጨማሪ ስጋቶች አስከትለዋል መባሉም በዘገባው ተካቷል። አስ