
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን ነፍሴ ሳር ምድር ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ግጭት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን ነፍሴሳር ምድር ወረዳ መርጦለማርያም ከተማ ዙርያ ደብረመድሀኒት በተባለች ስፍራ ከሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሁለቱ አካላት መካከል በተካሄደ ግጭት በትንሹ 5 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“በተለያዩ አቅጣጫወች ነው ውጊያ ስካሄድ የነበረው።” ያሉት ነዋሪው፤ የውጊያው መነሻ በአከባቢው የ “ፋኖ ታጣቂዎች የተለያዩ ተቋማትን መያዛቸውን” ተከትሎ “የተቋማቱ ንብረት እንዳይወሰድ በሚል በመከላከያ ሰራዊቱ እርምጃ መወሰድ በመጀመሩ” መሆኑን አስረድተዋል።
“መከላከያ የፋኖ ታጣቂዎች የተቋማትን ንብረቶች ሊወስድ እና ሊጠቀምባቸው ይችላል የሚል ፍራቻ ነበረው፤ እና ከባድ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ ነበረ” ብለዋል።
በዚህም በርካታ የተቋማት ንብረቶች ከመርጦለማርያም ዙርያ ካሉ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማዋ ሲጓጓዙ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም ዲሽቃን ጨምሮ በብሬል እና ስናይፐር በመሣሠሉ መሳሪያዎች ታግዞ ተካሄደ ባሉት ውጊያ ደብረመድሀኒት በተባለች ስፍራ 5 ሰዎች በተባራሪ ጥይት ተመተው ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በመርጦ ለማርያም ከተማ ዙርያ በሚገኙ ተንታ እና ደርጂ በተሰኙ ቀበሌዎች ውጊያዎች እንደተካሄዱ ገልጸው ትናንት ሀሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ማለዳ ላይ የ”መከላከያ ሰራዊት” በደርጂ ቀበሌ ት/ቤትን ጨምሮ በ”ፋኖ ታጣቂዎች” ቁጥጥር ስር የገቡ ተቋማትን ለማስለቀቅ መሞከሩን ተከትሎ የተኩስ ልውውጦች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም በርካታ ንጹሐን መቁሰላቸውን እንደሚያውቁ ገልጸው ይሁን እንጂ ምን ያህል ሰዎች እንደሆኑ አሃዛዊ መረጃው እንደሌላቸው አስረድተዋል።
በአከባቢው በመንግስት ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ውጊያ ዋነኛ ተጠቂዎች በአከባቢው የሚኖሩ ንጹሐን መሆናቸውን የሚገልጹት እኚሁ ነዋሪ፤ ሰራተኞች ወደ ስራ በሚሄዱበት፣ እናቶች ገበያ በወጡበት አጋጣሚ የሚከሰቱት ግጭቶች ለንጹሐን ድንገተኛ ሞት ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ግጭቱን ተከትሎ በነፍሴሳር ምድር ወረዳ ትምህርት እና ጤናን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ጠቅሰው በወረዳው ካሉ 35 ቀበሌዎች መካከል አሁን ላይ በከፊል አገልግሎትየሚሰጥባቸው 6ቱ ብቻ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ 29 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን አመልክተዋል።
ውጊያውን ተከትሎም በርካታ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው አከባቢውን እየለቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ አዲገነት በተባለች ቀበሌ ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂውች መካከል በተካሄደ ግጭት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ለደህንነቴ ሲባል ስሜ ባይጠቀስ ያሉ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
በአከባቢው ግጭቶች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመዱ መምጣታቸውን የሚገልጹት ነዋሪው አርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በቋሪት ወረዳ ዙርያ የምትገኘውን ገነት አቦ ቀበሌን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ውጊያ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በማግስቱ ማለትም ቅዳሜ ዕለት አንድ በአከባቢው ከብት ሲጠብቅ የነበረ ግለሰብ እና መንገደኛ የሆነች አንዲት ሴት በተባራሪ ጥይት ተመተው መሞታቸውን ገልጸዋል።
“አሁን አሁን የጥይት ድምጽ መስማት የየእለት ልምድ ሆኗል። ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰህ ለመስራት ቀርቶ ከቤትህም መውጣት ያስፈራል” ብለዋል።
ሌላኛው ስሜ ባይጠቀስ ያሉ ነዋሪ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ገነት አቦ ቀበሌ በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በነበረው ግጭት ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
ከተገደሉት መካከል ሁለቱ በእርሻ ስራቸው ላይ በነበሩበት ወቅት አንዲት ሴት ደግሞ መንገድ ላይ በምትጓዝበት ወቅት በተባራሪ ጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ገነት አቦ ቀበሌ ሙሉ በሙሉ “በመከላከያ ሰራዊቱ” ቁጥጥር ስር መግባቷን የሚገልጹት ነዋሪው፤ አያይዘውም በርካታ ሱቆች እና የንግድ ማዕከላት ላይ “በመንግሥት የጸጥታ አካላት ዝርፊያ እና ውድመት መፈጸሙን” ገልጸዋል።
“ሰራዊቱ ገነት አቦ እንደገባ ብዙ ነጋዴዎች የንግድ መደብሮቻቸውን ዘግተው ጠፍተዋል። የሰራዊት አባላቱ በየሱቁ እየገቡ የሚፈልጉቱን ይወስዳሉ። ልብስ መሸጫ ገብተው የሚወሰደውን ይጭናሉ። ሌላውን መንገድ ላይ በትነው እሳት ይለቁበታል። ቢራ መሸጫ ቤቶችም ገብተው የፈለጉትን ጭነው ይወስዳሉ” ብለዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ በምስራቅ ጎጃም ዞን መርጦለማርያም፣ አባይ በርሃ እስከ ወሎ አዋሳኝ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት፣ ገነት አቦና ሸንዲ ወንበርማ፣ በሰሜን ጎጃም ዞን ዘብስትና የጣና በለስ፣ ጭንባ ዳና ማርያም፣ በአዊ ዞን ጃዊ፣ ኑኑና አባይ ተፋሰስ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንትና ለይ ጋይንት፣ ሚካኤል ደብርና የበለሳ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኞች” ላይ እርምጃ ወስጃለሁ ሲል አስታውቋል።
በዚህም “1025 ፅንፈኛ ሲደመሰስ፣ 574 በማቁሰል በድኑ ይገለገልባቸው የነበሩ 10 ብሬን፣ 01 ስናይፐር፣ 126 ክለሽ፣ 88 ኋላ ቀር መሳሪያ፣ 9 ሸጉጥ፣ 34 ቦምብና 34 ትጥቅ ማርኬያለሁ” ብሏል።
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ግጭት በሰዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል።
በክልሉ በተደጋጋሚ ግጭት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ምዕራብ ጎጃም ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በርካታ ንጹሃን ሰዎች ህይወት አልፏል።
ለአብነትም በዞኑ ጃቢ ጠህናን ወረዳ ጅማት እንቆቅማ ቀበሌ አርብ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከለ በተካሄደ “በከባድ መሳሪያ” በታገዘ ውጊያ የ14 ዓመት ታዳጊ እና መነኩሴን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም በክልሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ሸባ በተሰኘች ቀበሌ በእርሻ አውድማ ላይ የነበሩ 11 ሰዎች “በመንግሥት የጸጥታ አካላት” መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በተጨማሪም ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም በዞኑ ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ “በፋኖ ታጣቂዎች” ለሁለት ወር ታግተው ከነበሩ 97 አመራሮች መካከል 37 የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች ተገድለዋል። አስ