ማህበራዊ ጉዳይጥልቅ ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ፕሮጀክት ሁለት ገጽታዎች፤ የለውጥ እና የመፈናቀል ታሪኮች

በይስሓቅ ኢንድሪስ  @Yishak_Endris

አዲስ አበባ፣ ጥር 5/ 2017 ዓ/ም፦ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀችት 40 ኮሎ ሜትር ያህል የሚረዝም ሲሆን ባሳለፍነው አመት ሚያዚያ ወር ተጀምሮ በመስከረም ወር ተጠናቋል።

ከተማዋ አሁን ላይ በመስከረም ወር የተጀመረውን አጠቃላይ ስፋቱ 2 ሺህ 817 ሄክታር እና 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ቦታ ላይ የሚገነባ የሁለተኛው የኮሪደር ልማት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በስምንት መስመሮች ላይ የሚከናወን ነው። በዚህም ከካዛንቺስ – እስጢፋኖስ – መስቀል አደባባይ – ሜክሲኮ – ቸርችል – አራት ኪሎ ኮሪደርና መልሶ ማልማት ሥራ 40 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚሸፍን የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ገልጸዋል። ከጫካ ፕሮጀክት (ሳውዝ ጌት)-መገናኛ – ሃያ ሁለት – መስቀል አደባባይ ኮሪደር ድግሞ 7 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል።

ከሲኤምሲ- ሰሚት- ጎሮ- ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደርና የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ኮሪደር 10 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው እንዲሁም ከሳር ቤት- ካርል አደባባይ- ብስራተ ገብርኤል- አቦ ማዞሪያ- ላፍቶ አደባባይ- ፉሪ አደባባይ ኮሪደር 15 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚሸፍን ጠቅሰው፤ የእንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር 21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከአራት ኪሎ- ሽሮ ሜዳ- እንጦጦ ማርያም- እጽዋት ማዕከል የሚገነባው ኮሪደር ደግሞ 13 ነጥብ 19 ኪሎ ሜት ርዝማኔን ይይዛል። ሌላኛው መስመር ከአንበሳ ጋራዥ _ ጎሮ ኮሪደር ልማት ሲሆን ይህም 16.58 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 3.1 ኪሎሜትር ርዝመት አለው።

ፕሮጀክቱ የመንገድ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የታክሲና አውቶቡስ ተርሚናሎች ግንባታና የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ የሚያካትት ነው።

በተጨማሪም የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች እና ሌሎችም በቴክኖሎጂ የተደገፉ መሠረተ-ልማቶች የሚከናወኑ መሆኑንም ተመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አዲስ ስታንዳርድ ኮዬ አደባባይ የሚደርሰው መንገድ ዳር እየተካሄደ ባለው ግንባታ ላይ ባደረገው የመስክ ምልከታ ተጀምሮ የነበረው የኮሪደር ልማት በአብዛኛው የተገባደደ ሲሆን በአደባባዩ ዙርያ የሚገኙትን የመንገድ ዳር ስፍራዎች የማስዋብ ስራዎች ተሰርተዋል።

በተለይ በማታ እነዚሁ የመንገድ ዳር መብራቶች ጎልተው የሚታዩ ሲሆን በእነዚሁ ስፍራዎች ሰዎች አረፍ የሚሉባቸው ወንበሮች ተቀምጠዋል።

በተጨማሪም ዝግዛግ በመስራት ከመሬት ወደ ሰማይ እየተምዘገዘገ ትዕይንት እንዲያሳይ ተደርጎ በተሰናዳው ፋውንቴን ዙርያ በርካታ ሰዎች ቆመው ሲመለከቱ እና ፎቶ ሲነሱ ማየት በተለይ ከአመሻሽ 12 ሰዓት በኋላ የተለመደ ነው።

አዲስ ስታንዳርድ ከኮዬ አደባባይ በመቀጠል ከጎሮ እስከ መብራት ሃይል ድረስ እየተካሄደ የሚገኘውን ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ግንባታ ሂደት ተመልክቷል።

ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ ከኮዬ ወደ መገናኛ ለመሄድ የነበረው ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ መቀነሱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

አቶ ፊሊሞን ዮሐንስ ነዋሪነታቸው በሸገር ከተማ አስተዳደር ኮዬ ፈጬ ክፍለከተማ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በተጀመረበት የጥቅምት ወር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደነበረ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።

“በጣም መከራ ነበረ ትራንስፖርት። እኔ አሁን 18 አቦ ማዞርያ አከባቢ ከምኖርበት በጠዋት 12:00 ተነስቼ መገናኛ የምደርሰው 3:00 አከባቢ ነበር። በተለይ እዚህ ጎሮ ጋር ሰላሳ እና አርባ ደቂቃ መኪናው ሳይንቀሳቀስ ልትቆም ትችላለህ። ኢቺን እንደምንም የጎሮዋን ካለፍክ በኋላ እንኳን እስከ መብራት ሃይል ድረስ እየተንፏቀክ ነበር የምትደርሰው።” ያሉት አቶ ፊሊሞን አሁን ላይ የትራንስፖርት መጨናነቁ እንደተስተካከለ ይገልጻሉ።

“አሁን ተስተካክሏል ከሞላ ጎደል። ያው ወትሮውንም እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው ሰዓታት ይታወቃሉ በተለይ የሥራ መግቢያ ሰዓታት ላይ የተለመደው የትራንስፖርት መጨናነቅ ይኖራል። እሱ የምትወጣበትን ሰዓት ካስተካከልክ ብዙ አትቸገርም። ከዚህ በፊት ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ ሰሞን ግን በጠዋት እንኳን ብትወጣ ጭንቅንቅ ነበረ የሚለው አሁን እሱ የለም።” ብለዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ምልከታውን ባካሄደባቸው ከጎሮ እስከ መብራት ኃይል በሚገኙ የመንገድ ዳር ስፍራዎች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ በፈረሱ የንግድ ቦታዎች፣ ሕንፃዎች እና መኖሪያ ቤቶች ተሞልቷል። ግንባታዎችን የሚያሳልጡ ቡልዶዘሮች እና የፈረሱ የቤት ቁሳቁሶችን የሚያስወግዱ ሰራተኞች በየአካባቢው ተሰማርተው ይስተዋላሉ።

አቶ መስኡድ ጀማል (ስማቸው የተቀየረ) በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ጠቀሜታ አለው ተብሎ እስከታሰበ ድረስ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

በለውጥ ላይ ባለችው ከተማ የድጋፍ እና ቅሬታ ድምጾች

አቶ መስኡድ በጎሮ የወርቅ ጌጣ ጌጥ መሸጫ ሱቅ ያላቸው ግለሰብ ሲሆኑ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ምክንያት ከሱቃቸውን ለቀው ሩቅ ወዳልሆነ ቦታ መዘዋወራቸውን ገልጸዋል።

አቶ መስኡድ መጀመሪያ ላይ ስጋት ገብቷቸው የነበረ ቢሆንም በፊት ከነበሩበት ሱቅ ይልቅ አዲስ የተዘዋወሩበት ሱቅ ላይ “የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ” መኖሩን ይናገራሉ።

“በከተማዋ በተለያዩ ሥፍራዎች ከኮሪደሩ ልማት በኋላ የታየው የመንገዶች መስፋት እንዲሁም ውበት እሳቸው ባሉበት ቦታ ላይም ሊሆን መቃረቡ አስደስቶኛል” ብለዋል።

በጎሮ አካባቢ ያለው የኮሪደር ልማት አሁናዊ ገጸታ፤ ፎቶ _ አዲስ ስታንዳርድ

ከዚህ በተቃራኒ ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በየረር ሰፈር ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ሁለተኛውን ምዕራፍ  የኮሪደር ፕሮጀክት ተከትሎ “ያለምንም ቅድመ-ማስጠንቀቂያ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ባርና ሬስቶራንት እንደፈረሰባቸው” ጠቁመዋል።

“የረር አለማየሁ ህንፃ አከባቢ ከፍ ብሎ በኮሪደር ልማት ምክንያት አንድ አምስት አባወራ ተነስተዋል ከእኛ መደዳ የነበሩ ናቸው። አንደኛው መለስተኛ ክሊኒክ የነበረ አለ። ሌላው የኔ ባርና ሬስቶራንት አለ። በስሬ ከሰባት ያላነሱ ሰራተኞች ነበር የማስተዳድረው፤ ምንም ባልጠበቅነው ጊዜ አስነሱን” ብለዋል።

በዚህም ላለፉት ሁለት ወር ስራ እየሰሩ አለምሆኑን ገልጸው በሰዓቱ በጽሑፍም ሆነ በማስታወቂያ የተሰጠ ማሳሰቢያ አለመኖሩን ተናግረዋል።

“221 ካሬ ላይ ያረፈ ቦታ ላይ የሰራሁት ሬስቶራንት እና ሱቆች ነው በሶስት ወሩ ነው የፈረሰው።” ያለው ነዋሪው አቃዎቹን እንዲያወጡ ሶስት ቀን በቻ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።  ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ምንም አይነት ስራ ባለመሆኑ ስለሚከፍሉት ዓመታዊ ግብር በእጅጉ እንደሚያሳስባቸውም አስረድተዋል።።

በተጨማሪም አሁን ላይ ከዚህ ቀደም ሲሰሩበት ከነበረው ቦታ ጀርባ ካለ ግቢ በ20ሺህ ብር ተከራይተው መኖር እንደጀመሩ ገልጸዋል።

ምትክ ወይም ተለዋጭ ቦታን በተመለከተም ግምት እንደሚሰራላቸውና ዕጣ እንደሚወጣላቸው መነገራቸውን ገልጸው ይሁን እንጂ ቃል የተገባላቸው ግምት ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

“የእኛ ቦታ አሁን 221 ካሬ ነበረ። ነገር ግን ምትክ እንደሚሰጠን ቃል የተገባልን 150 ካሬ ነው። ይሁን እንጂ በሚዲያ ስንሰማ የነበረው በካርታ ላይ ያለው ሙሉ መሬት እንደሚሰጥ ነበረ። በዚህም ማዕከል ሄጄ  ቅሬታ እንዳለኝ አስታውቅያለሁ።” ብለዋል።

እንዲሁም ካሣን በተመለከተ  “ቃል የተገባልን ገንዘብ ይሰጣል ተብለናል ግምትም ገምተው ሄደዋል እስከአሁን ግን ምንም ነገር የለም።” ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም እቃ ለማውጣት እና ለማዘዋወር የማስጫኛ (የመኪና ኪራይ) እንዲሁም ለመኖርያ ኪራይ ክፍያ እንደሚሰጣቸው ቢነገራቸውም እስከ አሁን ድረስ ምንም ነገር አለመኖሩን አመልክተዋል።

የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ፕሮጀክት አስመልክተው መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ በልማቱ ዙሪያ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ተነሺዎችን የማወያየት ሰፊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በልማቱ ለሚነሱ የግል ባለይዞታዎችም 5 ቢሊየን ብር የሚደርስ ካሳ በጀት መያዙን በመግለጽ 100 ሄክታር የሚጠጋ ምትክ መሬትና የሁለት አመት የቤት ኪራይ ክፍያም እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል፡፡

ለልማት ተነሺ ደግሞ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ መስሪያ ቦታዎች የንግድ ቤቶችና ሱቆች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ አዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉት እና ስማቸውም ሆነ የንግድ ቤታቸው መጠሪያ እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ በበኩላቸው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ካሳ እና ምትክ ቦታ እንዲነሱ መደረጋቸውን ይገልጻሉ።

የረር አከባቢ የአትክልት ቤት ከፍተው ሲሰሩ እንደነበረ የገለጹት ነዋሪ እንደገለጹት “ከመርካቶ ለአትክልት ቤቴ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን እያስመጣሁ በነበረበት በዛው ዕለት እቃሽን አውጪ ተባልኩ” ስትል በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ምትክ ቦታ እና ካሣን በተመለከተም እንደሚሰጥ ከተለያዩ ሚዲያዎች መስማታቸውን ገልጸው ነገር ግን እስከአሁን ተግባራዊ የሆነ ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል።

አክለውም “ነጋዴው ግብር ከፋይ ነው፤ አሁን የግማሽ ዓመት አልሰራንም። ምን ልንከፍል ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።  “ልማትን የሚጠላ የለም” ያሉት ነዋሪዋ “ከጅምሩ የተጠና ስራ ቢኖር ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።

 ከትርምስ ወደ ማራኪነት

በሌላ በኩል አዲስ ስታንዳርድ ቅኝት ባደረገባት ፒያሣ አከባቢ ያገኘናቸው ነጋዴዎች በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ፕሮጀክት ከነበሩበት አከባቢ ቢነሱም ምትክ ቦታ ተሰጥቷቸው ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም በመነጸር እና በሰዓት ንግድ ላይ የተሰማራችው ሜሮን መስፍን በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ሣቢያ ከነበረችበት እና “መነጸር ተራ” ተብሎ ከሚጠራው አከባቢ መነሳቷን ታስታውሳለች።

እሷን ጨምሮ ከእሷ ጋራ አብረው ሲሰሩ የነበሩ ሌሎች ሰዎች አሁን በምትገኝበት በአራዳ የገበያ ማዕከል አከባቢ ቦታ ተሰጥቷቸው ሥራ መጀመራቸውን ገልጻለች።

ሌላኛው አራዳ ህንጻ ፊት ለፊት ያገኘናቸው የወርቅ ነጋዴ በበኩላቸው የመጀመሪያውን ዙር የኮሪደሪ ፕሮጀክት ተከትሎ ሱቃቸው ፈርሶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እንደአዲስ ወደ ስራ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

እሳቸውን ጨምሮ በመደዳ የሚታዩት ወርቅ ቤቶች እንዲሁም በአምፒር ሲኒማ አከባቢ የሚታወቁት ወርቅ ቤቶች ተከፍተው ስራ መጀመራቸውን አዲስ ስታንዳርድ ባደረገው ቅኝት ለመታዘብ ችሏል።

እኚሁ ግለሰብ አክለውም “ሌሎች እዚህ አከባቢ የሚታወቁ ወርቅ ቤቶች ወደ 4ኪሎ አምባሳደር በመሄድ ተከራይተው ስራ የጀመሩም አሉ።” ብለዋል።

ከፕሮጀክቱ በኋላ ስላለው የንግድ እንቅስቃሴ የተጠየቁት እኚህ ግለሰብ “ጥሩ ነው። እየሰራን ነው። የልማት ደጋፊ ነን።” ሲሉ በአጭሩ መልሰዋል።

አዲስ ስታንዳርድ በፒያሣ በመዟዟር ቅኝት ባደረገበት ወቅት በርካታ ሰዎች በተለይም በውሃ ፋውንቴኖች አከባቢ ፎቶ ሲነሱ፤  በመንገድ ዳር በተሰናዱ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ጊዜ ሲያሳልፉ ማየት ችሏል።

በተጨማሪም 4ኪሎ ድልድዩ ከነበረበት ስፍራ ወደ ላይ እስከ 6ኪሎ ፕሮጀክቱ በስፋት እየተከናወነ ሲሆን ከተቆፈሩ መንገዶች አጠገብ የአሸዋ ክምሮች፣ ግሬደሮች እና ቡልዶዘሮች እንዲሁም የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በስፋት ይታያል።

4ኪሎ ከዚህ በፊት የምትታወቅበት የመጽሐፍት እና የመጽሔት ሻጮች እንደ በፊቱ በመደዳ ባይታዩም አልፎ አልፎ በተለይም በህንጻዎች ውስጥ ባሉ መግቢያ ወይም ባዶ ቦታዎች እንዲሁም ከህንጻዎች አጠገብ ለእግረኞች መተላለፊያ ተብለው በተሰሩ ኮሪደሮች አጠገብ ተነጣጥለው ይታያሉ።

በመዲናዋ በመከናወን ላይ የሚገኘው የኮሪደር ፕሮጀክት በቅርቡ በተለያዩ የክልል ከተሞች በስፋት እየተካሄደም ይገኛል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button