አዲስ አበባ፣ ጥር 5/ 2017 ዓ/ም፦ ብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና መሥጠት መጀመሩን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል “ጥያቄዎቻቸዉን በሀይል ለማሳካት ታጥቀዉ ሲንቀሣቀሱ ነበር” ያላቸውና በቅርቡ ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈፀም በማዕከላት ከተሰባሰቡት መካከል በአዋሽ ቢሾላ የተሃድሶ ማዕከል ለሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን ገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ያስረከቧቸው መሳሪያዎችን ለመከላከያ ተወካዮች የማስረከብ ስነ-ስርዓት እና በስምምነቱ መሰረት የቀድሞ ታጣቂዎችን ዝርዝር የያዘ የሰነድ ርክክብ መከናወኑን ከኮሚሽኑ የማህበራዊ ትስስር-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በወቅቱ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደገለጹት ኮሚሽኑ በፕሮግራሙ የሚያልፉ ተሳታፊዎችን የቀድሞ ታጣቂ መሆናቸውን የማረጋገጥ፣ የመመዝገብና ዲጂታል መታወቂያ መስጠት፣ የሳይኮ ሶሻልና የሲቪክስ የተሃድሶ ሥልጠና እንዲሁም የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
አክለውም “በቀጣይ ወደ ማህበረሰቡ ስትቀላቀሉ የሠላምና የልማት አጋርነታችሁን ከማረጋገጥ ባሻገር የሰላም አምባሳደር ጭምር በመሆን አርዓያነታችሁን እንድትወጡ” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በቡርቃ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።
በወቅቱ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በበኩላቸው “የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣታቸው ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል” ብለዋል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎች መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ እና ምዝገባ፣ የተሐድሶ ስልጠና እና የመልሶ ማቋቋም ሂደት እንደሚያከናውን ተጠቁሟል።
በስልጠናው ሂደት የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎችም የተሐድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ሰላማዊ ህይወትን የሚመሩ ይሆናል ተብሏል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች የተሃድሶ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱም ተመላክቷል።
ስልጠናውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉም መደበኛ ህይወታቸውን መምራት የሚያስችል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል።
ይህ የሆነው ታህሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ኮሚሽኑ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በክልሉ ያሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀልና መልሶ ለማቋቋም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማካሄዱን ተከትሎ ነው።
ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ከ5,000 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች የመልሶ ማቋቋም ስልጠና ጨርሰው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል። አስ