አዲስ አበባ፣ ጥር 17/ 2017 ዓ/ም፦ አርባ አራት የሚሆኑ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ኒቃብ ለብሰው ወደ ግቢው እንዳይገቡ እንደተከለከሉና አንዳንዶቹም ከአምስት ቀናት በላይ በመስጂዱ ውስጥ ለመቆየት መገደዳቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተማሪዎች፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ኒቃብ መልበስ ይፈቀድ የነበረ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ “የደህንነት ስጋትን” በመጥቀስ ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ ኒቃብ መልበስን እንደከለከለ ተናግረዋል።
ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች አንድ ተማሪ፤ እገዳው ከአንድ ወር ገደማ በፊት መጀመሩን ገልጻ ነገር ግን መጀመሪያ ላይ በጥብቅ አልተተገበረም ብላለች።
“መጀመሪያ ላይ በጥብቅ አይተገበርም ነበር።” ያለችው ተማሪዋ አክላ መታወቂያ ካርዶቻችን ይወሰዱ ጀመር፣ ሆኖም የተማሪ መሪዎች ጣልቃ ሲገቡ ጠባቂዎቹ የወሰዱትን መታወቂያ መለሱልን።” ስትል ስለ ሁኔታው ትናገራለች።
ተማሪዋ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጉዳዩ መባባሱን ገልጻለች።
“አንዷ ጓደኛችን ከካምፓስ ውጭ ምግብ ከገዛች በኋላ ተመልሳ ስትመጣ ያደረገችውን ጥቁር ማስክ አውልቃ ፊቷን እንድታሳይ ተነገራት” ስትል ገልጻ፤ “ሂጃብ ስትለብስ ጥቁር ማስክ ማድረግ እንደማትችል ተነገራት” ብላለች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኒቃብ ለብሰው የሚማሩ ተማሪዎች በተደጋጋሚ እንዲያወልቁ ወይም ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ተነግሯቸዋል ስትል አስረድታለች።
በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በርካታ የጽሑፍ ቅሬታዎችን ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ እንዳላገኙ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግራለች።
ለደህንነቷ በመስጋት ስሟን እንዳንጠቀስ የጠየቀች ሌላ የዩኒቨርስቲው ተማሪ በበኩሏ “ዩኒቨርሲቲው መደበኛ ቅሬታችንን ችላ ብሎታል” ስትል ገልጻለች።
የቅሬታ ደብዳቤያችን “በቅርቡ መልስ እንሰጣለን በሚል ሰበብ ውድቅ ተደርጓል፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት መፍትሄ አልተሰጠም” በማለት ሁኔታውን አስረድታለች ።
ተማሪዋ ሰኞ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም የሙስሊም ተማሪዎች ማህበር ሊቀመንበር ተጠርተው “ጥቁር ማስክ ወይም ኒቃብ የሚለብስ ማንኛውም ሰው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ወይም እንዲወጣ እንደማይፈቀድለት” ከተነገረው በኋላ ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን አመልክታለች።
በተጨማሪ ሰኞ ምሽት ላይ ጥቁር ማስክ ለብሰው በክፍል ውስጥ የተገኙ ተማሪዎች ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ እንዲገቡ እንደተፈቀደላቸው ገልጻለች።
“ይሁን እንጂ ኒቃብ የለበስን ሰባት ተማሪዎች ወደ ግቢው መግባት ተከልክለን ከአምስት ቀናት በላይ በመስጂድ ውስጥ ቆይተናል።” ብላለች።
በዲላ ዩኒቨርስቲ የሙስሊም ተማሪዎች ማህበር ሊቀመንበር የሆነው ኑረዲን አብደላ በበኩሉ ጉዳዩን ከዩኒቨርስቲው የስራ ሃላፊዎች ጋር በጽሑፍም ሆነ በአካል ለመፍታት የተደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶች መፍትሄ አለማምጣታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
አክሎም “በርካታ ሙስሊም ተማሪዎች ላለፉት አምስት ቀናት በመስጂድ ውስጥ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ ለፈተና መቅረብም ሆነ የሚጠበቅባቸውን አሳይመንት ለማጠናቀቅ አልቻሉም” ብሏል።
በተጨማሪም ጥቁር ማስክ ለብሰው ወደ ግቢው ለመግባት የሞከሩ ተማሪዎች ከግቢው ደህንነት ሰራተኞች ማስፈራሪያ ገጥሟቸዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ኢስላማዊ አልባሳት ስለለበሱ ብቻ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው የሚጠይቅ የመጨረሻ ያለውን ደብዳቤ ለትምህርት ሚኒስቴር ጽፏል፡፡
ምክር ቤቱ ከኢስላማዊ አለባበስ ጋር በተያያዘ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሚደርስባቸውን ከፍተኛ ጫናና ከትምህርት መፈናቀል በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝ ውይይቶች ሲያደርግ መቆየቱንና በዚህ ወር ብቻ ለትምህርት ሚኒስቴር ሶስት ጊዜ ደብዳቤዎችን መጻፉን ጠቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር እስከ አሁን ተገቢ ምላሽ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳላገኘና አሁንም ችግሩ በዲላ ዩንቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ መፈፀሙን አመላክቷል፡፡
ምክር ቤቱ የመጨረሻ ባለው በዚህ ደብዳቤ ኢስላማዊ ልብስ ስለለበሱ ብቻ ትምህርት የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተገፎ ወደ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ የተከለከሉ የዲላ ዩንቨርስቲ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በአፋጣኝ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱና ለችግሩ ዘላቂ አስተዳደራዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጠይቋል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩን በተመለከተ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ባሰፈረው አጭር ጽሑፍ “ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ ታግደዋል” የሚሉ ክሶችን አስተባብሎ የተሰራጩትን ዘገባዎች “ሐሰት” ብሏል።
“ዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን ሂጃብ መልበስ የተከለከለ አለመሆኑን ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን” ሲል አክሏል።
በቅርቡ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የታደሙበት ሰልፍ መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።
ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሂጃብ ለመልበስ የሚያስችላቸውን መብት ያረጋግጣሉ የተባሉትን የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ መመሪያዎችን በመተግበር ረገድ እየታዩ ናቸው ያሏቸውን መለሳለስ በመቃወም ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ አደም አብዱልቃድር “ሴት ልጆቻችን ከፍርድ ቤት እና ከትምህርት ቢሮው በግልጽ የተላለፉ መመሪያዎችንና ውሳኔዎች ቢኖሩም አሁንም ትምህርት እንዳይከታተሉ እየተከለከሉ ነው” ብለዋል።
አክለውም “በክልሉ እስልምና ለብዙ መቶ ዘመናት የባህል አካል በሆነበት ሁኔታ ይህ በጣም የሚያሳስብ ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል።አስ