አዲስ አበባ፣ ጥር 15/2017 ዓ.ም፡- በምርጫ ቦርድ እወቅና ተሰጥቶት በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ በሚያቋቁመው የአማካሪ ምክር ቤት እንደማይሳተፍ ትላንት ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የግዜያዊ አስተዳደሩ በጻፈለት ደብዳቤ የአማካሪ ምክር ቤቱ አባላት የሚሆኑ ስድስት የፓርቲው ተወካዮች ስም ዝርዝር እንዲላክለት መጠየቁን ያስታወቀው ፓርቲው የአማካሪ መክር ቤቱን ለማቋቋም በሚል ተሰይሞ የነበረው ኮሚቴ ካቀረበው ምክር ሃሳብ ባፈነገጠ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የማቋቋሚያ ደንቦቹን ለራሱ በሚያመቸው መንገድ በመተካት እየተንቀሳቀሰ ነው ሲል ኮንኗል።
ባሳለፍነው አመት አጋማሸ ግዚያዊ አስተዳደሩ በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማሕበራት፣ የፀጥታ ሐይሎች እና ሌሎች አካላትን የሚያካትት አማካሪ ምክር ቤት ለማቋቋም መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል።
በዚህም ውሳኔ መሰረት ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከባለሞያተኞች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለሶስት ወራት ከሁለት ሳምንታት ባካሄድነው ምክክር ስለ አማካሪ ምክር ቤቱ የደረሰበትን ውሳኔ አቅርቧል።
የምክር ቤቱ ማቋቋሚያ ሰነድ በማዘጋጀት ስራው ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሳልሳይ ወያነ ትግራይን ጨምሮ በትግራይ ክልል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓረና ትግራይ ለሉአለዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ዓሲምባ ዴሞክራስያዊ ፖርቲ ምክር ቤቱን ለማቋቋም ሲደረጉ የነበሩ በርካታ ውይይቶች ወደጎን በገፋ መልኩ፣ በግዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ቀርቦ የጸደቀው ሰነድ በርካታ ጉድለቶች ያሉበት ነው ሲሉ መተቸታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በኮሚቴው የቀረበውን ምክረ ሃሳብ በተለይም የምክር ቤቱ ተጠሪነት፣ የአባላቱ አመራረጥ፣ የምክር ቤቱ ሃላፊነት እና ተግባር፣ የምክር ቤቱ ተቋማዊ ቅርጽ፣ በስሩ የሚቋቋሙት ኮሚቴዎችን አስመልክቶ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ነጥቦች ወደ ጎን በመተው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለራሱ የሚያመቸውን ብቻ በማካተት ለማቋቋም እየጣረ ነው ሲል ተችቷል።
ፓርቲያችን ሳልሳይ ወያነ ይህንን አካሄድ አይቀበለውመ ሲል አስታውቋል፤ መስተካከል አለባቸው ያላቸውነ ነጥቦች በዝርዝር በደብዳቤው ያካተተው ፓርቲው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ታሪካዊ ስህተት ከመሰራት ይቆጠብ ሲል ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል።
የአማካሪ ምክር ቤቱ አሳታፊነት በተመለከተ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢ የጸደቀው ሰነድ ለህወሓት 48 ተወካዮች እንዲኖሩት በማድረግ ለሌሎቹ የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ግን እያንዳነዳቸው 6 ተወካዮች እንዲኖራቸው ያደርጋል ሲል ተችቷል።
የአንድ ፓርቲ የበላይነትን ለማስቀጠል እየተደረገ ያለ ጥረት ነው ሲል ኮንኗል።
የአማካሪ ምክር ቤቱን ለማቋቋም የተሰየመው ኮሚቴ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ የምክር ቤቱ ተጠሪነት ለህሊና፣ ለህግ እና ለትግራይ ህዝብ ሁኖ እያለ በጸደቀው ደንብ ግን ተጠሪነቱን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት እንዲሆን መደረጉን በማስታወቀ አልቀበለውም ብሏል።
በተጨማሪም በጊዜያዊ አስተዳደሩ የጸደቀው የአማካሪ ምክር ቤቱ ማቋቋሚያ ሰነድ ላይ “በፕሬዝዳንቱ አነሳሽነት ምክር ቤቱ ሊበተን ይችላል” የሚል ድንጋጌ መቀመጡን በመጥቀስ አልቀበለውም ሲል አስታውቋል።
በአጠቃላይ አማካሪ ምክር ቤቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጎ እየተቋቋመ በመሆኑ አልቀበለውም አልሳተፍ ሲል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) በትግራይ አስቸኳይ ምርጫ ተካሂዶ በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት እንዲኖሩት ሲል ትላነት ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
“የትግራይ ህዝብ እንደ ፌደሬሽን አባልነቱ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት 38 ወንበሮች ያሉት ቢሆንም ከጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተወክሎ አያውቅም” ሲል አስታውሷል።
ባለፉት አራት ዓመታት በፓርላማው እና በፌደሬሽን ምክርቤቶች የሚተላለፉ ውሳኔዎች የትግራይ ህዝብን ፍላጎቶች ያካተቱ አልነበሩም ሲል ገልጿል።
ስለዚህ “አስቸኳይ ምርጫ በማካሄድ የትግራይ ህዝብ ጉዳዮችን በእንደራሴዎቹ እንዲወስን በህዝብ ተወካዮች እንዲወከል እንዲደረግ” ሲል ጠይቋል።
“ህጋዊና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ የትግራይ ህዝብ በእንደራሴዎቹ እስኪወከል ድረስ ሁሉንም ሕጋዊ ፓርቲዎች ያካተተ የመማክርት ምክርቤት እንዲቋቋም” ሲልም አሳስቧል። አስ