ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኮሚሽኑ በትግራይ እና አማራ ክልሎች ለመስራት አዳጋች አንደሆነበት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት እንዲሁም ትግራይ ክልል ያለው “ወቅታዊ ሁኔታ” ስራዬን አዳጋች አድርጎታል ሲል ገልጿል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጥበቡ ታደሰ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በአማራ ክልል ተጠናክረው በቀጠሉት ግጭቶች ሳቢያ አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች መከናወን አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

“ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ጥረት አድርጓል” ያሉት ቃል አቀባዩ ነገር ግን በክልሉ ባለው “ወቅታዊ ድባብ የተነሳ በበርካታ ወረዳዎች የተባባሪ አካላት ሥልጠናን ማከናወን አለመቻሉን” ጠቁመዋል።

አክለውም የምክክር ሂደት አንፃራዊ ሰላም እንደሚያስፈልገው ገልጸው ነገር ግን “አሁን ላይ የተሟላ ሰላም የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም ተባባሪ አካላትን ለመለየት እና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ አስፈላጊውን ሥልጠና ለማከናወን ተግዳሮት መፍጠሩን አብራርተዋል።

በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን ስልጠና እንዲሰጣቸው ጥረት መደረጉን የገለጹት ቃለአቀባዩ ሆኖም በታሰበው ግዜ ሥራዎች እየተከናወኑ እንዳልሆነ አመላክተዋል።

በአማራ ክልል እየተካሄዱ የሚገኙ በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች የሚቀጥሉ ከሆነና ተሳታፊ አካላት ያልተለየባቸው እንዲሁም የምክክር ሂደቱ በሚገባ ያልተከናወነባቸው አከባቢዎችን በተመለከተ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምክር ቤት ውይይት እያደረገ እንደሚገኝና የሚቀመጡ አቅጣጫዎች ካሉም ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ቃልአቀባዩ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በተመሳሳይ ኮሚሽኑን ለተለያዩ ተግዳሮቶች እንደዳረገው ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል ከሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ውይይት ለማድረግ ጥረት መደረጉን የገለጹት አቶ ጥበቡ ታደሰ፤ “ነገር ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የሚደረገው የምክክር ሂደት ይበልጥ የተሳካ እንዲሆን አንዳንድ ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ የሚል ሃሳብ ስላለው እነዚህ ጉዳዮች ተስተካክለው ምክክር የሚካሄድበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ነን።” ብለዋል።

በአንጻሩ ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ “በተሳካ ሁኔታ” እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button