አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ተጠልለው በሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ላይ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸሙባቸው ነው ሲል ሂዩማን ራይት ዎች ባወጣው ሪፖርት ኮነነ።
መንግስት በበኩሉ መሰረተ ቢስ እና ፍጹም ሀሰት ነው ሲል ምላሽ መስጠቱን ሂዩማን ራይት ዎች በሪፖርቱ አካቷል።
በአማራ ክልል ሰሜን ምዕራብ አከባቢው ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ መጠለያ ካምፖች እና በአካባቢው በሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞችን ለከፋ ስጋት እና አደጋ ዳርጓቸዋል ሲል ሂዩማን ራይት ዎች አስታወቀ።
በአከባቢው የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞች ለአንድ አመት በዘለቀው ግጭት ሳቢያ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እና ሚሊሻዎች ሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው ነበር ሲል የገለጸው ሂዩማንራይት ዎች ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ደግሞ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ሰብአዊ መብት ጥሰት በስደተኞቹ ላይ እየፈጸሙባቸው ነው ሲል ኮንኗል።
መንግስት ለስደተኞቹ የሚሰጠውን ከለላ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲልም ተቋሙ ዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት አሳስቧል።
የመንግስት ተቋም የሆነው የስደተኞች እና ከስደት ተመላኞች አገልግሎት በጉዳዩ ዙሪያ ለሂዩማን ራይት ዎች በሰጠው ምላሽ “በሱዳን ስደተኞች ላይ በአካባቢው ሚሊሻዎች እና መደበኛ ባልሆኑ ቡድኖች በደል፣ ግድያ፣ ዘረፋ፣ ወዘተ ተፈጽሞባቸዋል መባሉ መሰረተ ቢስ እና ስህተት ነው” ማለቱን ሪፖርቱ አካቷል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላኞች አገልግሎት አክሎም የኢትዮጵያ መንግስት “በስደተኞች ላይ ምንም አይነት የሰብአዊ በደል በሚፈጽሙ አካላት ላይ መንግስት ትዕግስት የለውም” የሚል ምላሽ መስጠቱም ተገልጿል’
በሱዳን መንግስት ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተነሳበት ሚያዚያ ወር 2015 ጀምሮ በርካታ ሱዳናውያን እና በሱዳን ይኖሩ የነበሩ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመሸሽ ተጠልለው እንደሚገኙ ተቋሙ በመግለጫው አስታወቋል።
ብዙዎቹ ስደተኞች መጀመሪያ ላይ በአማራ ክልል ወደሚገኙ ሁለት የስደተኞች ካምፖች መጠለላቸውን የጠቆመው ሂዩማን ራየት ዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እና ሚሊሻዎች በስደተኞቹ ላይ የጉልበት ስራ ከማሰማራት ጀምሮ ግድያ፣ ድብደባ፣ ዝርፊያ፣ እገታ ፈጽመውባቸዋል ሲል ገልጿል።
“በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ከአንድ አመት በላይ በተለያዩ ታጣቂዎች ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይተዋል” ሲሉ የተቋሙ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ለተሺያ ባደር ገልጸው
“እነዚህ ስደተኞች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያደረጋቸው አስከፊ ጥቃት ስለደረሰባቸው በመሆኑ ተጨማሪ ስቃይ ሳይሆን በአፋጣኝ ከለላ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል በሚገኙ ሶስት መጠለያ ካምፖች የሚገኙ 20 ስደተኞችን በስልክ ቃለመጠይቅ በማድረግ፣ ሱዳናውያን የረድኤት ድርጅት ሰራተኞችን እና አክቲቪስቶችን በማነጋገር እንዲሁም የመጠለያ ካምፖቹን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ የሳትላይት ምስሎችን እንዲሁም በኦንላይ የተለቀቁ የቪዲዮዎችን በመጠቀም ለመተንተን መሞከሩን አስታውቋል።
የመጀመሪያ ግኝቱንም ለመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን እና ለኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት መላኩን ጠቁሟል፤ ከተቋማቱ ምላሽ ማግኘቱንም አስታውቋል።
ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብ ጎንደር በሚገኙ ሁለት መጠለያ ካምፖች አውላላ አና ኩሙር ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሶስት ስደተኞች ከመግደላቸው በተጨማሪ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በስደተኞቹ ላይ መፈጸማቸውን ገልጿል።
መጠለያ ካምፖቹ የተቋቋሙት በአማራ ክልል በመንግስት እና በፋኖ ሀይሎች መካከል ግጭት ከመፈጠሩ በፊት በአከባቢው የሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ግጭት በሚያስተናግዱ ቦታዎች ላይ ነው ሲል ገልጿል፤ በአማራ እና ቅማንት ማህበረሰቦች መካከል ግጭት የሚስተዋልበት አከባቢ ነው ብሏል።
በመጠለያ ካምፖቹ ላይም መንግስት በቂ የጸጥታ ሀይል አላሰማራም ሲል ተችቷል።
በመጠለያዎቹ ተጠልለው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ደርሸበታለሁ ሲል የገለጸው ሂዩማን ራይት ዎች በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠኝ ምላሽ ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት በፈቃዳቸው ነው ማለቱንም በሪፖርቱ አካቷል።
ነገር ግን ከበርካታ ስደተኞ ያገኘሁት ምክንያት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በጉልበት ወደ ሱዳን እንዲመለሱ ስላደረጓቸው መሆኑን ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ “ስደተኞችን ወደ ሱዳን ለመመለስ ምንም ምክንያት የለም ምክንያቱም እዚያ ያለው ሁኔታ ወደ አገራቸው መመለስን አይፈቅድም” የሚል ምላሽ ለሂዩማን ራይት ዎች ምላሽ መስጠቱን ሪፖርቱ አካቷል።
ሁሉም ወታደራዊ ሃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች በስደተኞች ላይ የሚፈጽሙትን ሰብአዊ መብት ጥሰት ማቆም አለባቸው ሲል ያሳሰበው ተቋሙ እነዚህ ሀይሎች ከካምፖቹ ለቀው መውጣት አለባቸው፣ የሰብአዊ እርዳታን በአስተማማኝ መልኩ ለማድረስ የሚያመች ሁኔታዎችንም መፍጠር አለባቸው ሲል አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት አጋር የሆኑ አለም አቀፍ ተቋማት በሀገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች በቂ ጥበቃ እንዲያደርግ፣ በግዳጀ ወደ ሀገራች መመለስን እንዲያቆም፣ ሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ እና ስደተኞቹን የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ ወዳለበት ቦታ እንዲያሰፍራቸው የኢትዮጵያን መንግስት ላይ ጫና መፍጠር አለባቸው ሲልም ጠይቋል።
በአሁኑ ወቅት ከ90ሺ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በኢትዮጵያ ተጠልለው እንዲገኙ አለምአቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ የሆነው ሂዩማን ራይት ዎች አስታውቋል።
በአማራ ክልል በሱዳናውያን መጠለያ ካምፕ አቅራቢያ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መገደላቸው፣ ስደተኞች መጎዳታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በአብዛኛው ሱዳናዊ ስደተኞችን ባስጠለለው በኩመር የመጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ፖሊሶች መገደላቸውን እንዲሁም በርካቶች መቁሰላቸውን በዘገባው ተካቷል። አስ