ዜናፖለቲካ

ዜና: “አቶ ጌታቸው ረዳን በሚተኳቸው ተሿሚ ዙሪያ ከፌደራል መንግስቱ ጋረ እየተነጋገርን ነው” - ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም፡- በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት የጽህፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረግዚአብሔር ፓርቲያቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ማንሳቱን አስታውሰው እሳቸው በሚተካ ተሿሚ ዙሪያ ከፌደራል መንግስቱ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገር ነው ሲሉ አስታወቁ።

ከፓርቲው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ዋና ጸሃፊዋ በሰጡት ማብራሪያ “የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የተሾሙት በጋራ ስምምነት በመሆኑ አንድ አካል በፕሬዚዳንቱ ላይ እምነት ካጣ ለማውረድ ምንም ችግር የለውም” ሲሉ ገልጸዋል።

“ሁለታችንም ያመንበት ነው የሚሆነው፣ አንዳችን ካላመንበት አይሆንም” ብለዋል፤ ማን ይተካ በሚለው ዙሪያ መነጋገር አለብን ሲሉ ጠቁመዋል።

“በፓርቲያችን መግለጫ ላይ እንደተገለጸው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት በሚተኩት ተሿሚ ዙሪያ ከፌደራል መንግስቱ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ነው ያልነው” ሲሉ የገለጹት ፈትለወርቅ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት “ማንሳቱን አንስተነዋል፣ ማን ይተካቸው በሚለው ዙሪያ እየተነጋገርን ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

ህወሓት በግዜያዊ አስተዳደሩ ያለው ኮታ በመጠቀም የካቢኔ ተሿሚዎቹ ላይ ምደባ በማድረጉ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሊያፈርስ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ፍጹም ሀሰት ነው ማለታቸውንም ፓርቲው ባጋራው መረጃ ላይ አመላክቷል።

በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት የጽህፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረግዚአብሔር የጊዜያዊ አስተዳደሩ አጠቃላይ 27 ወንበሮች አሉት ሲሉ ገልጸው ህወሓትን የሚመለከተው 14ቱ ብቻ ናቸው ሲሉ ጠቁመዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩን የመሰረቱት ከትግራይ ሰራዊት፣ ከምሁራን እና ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ የተመደቡ 13 የካቢኔው ተሿሚዎች አሁንም በቦታቸው አሉ ሲሉ ያብራሩት ዋና ጻሃፊዋ የህወሓትም ቢሆን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምስረታ ወቅት የተመደቡ 6 ተሿሚዎች ቀጥለዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ይህም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ያሉ እና የቀጠሉ የካቤኒ አባላትን 19 ያደርሰዋል ሲሉ ጠቁመው ከዚህ ውጭ ደግሞ 3 የሚሆኑ የካቢኔ አባላት ቀደም ብለው ቦታውን በመልቀቃቸው በነሱ ምትክ ነው ሰው የተመደበው ብለዋል።

በአጠቃላይ በቅርቡ ፓርቲው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ያደረጋቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት 5 ብቻ ናቸው ሲሉ ገልጸው መፈነቅለ መንግስት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ አየተካሄደ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ፍጹም ሃሰት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ህወሓትን አትወክሉም ውረዱ ብለን ያነሳናቸው ፕሬዝዳንቱን አቶ ጌታቸው ረዳን፣ በየነ ምክሩ፣ ፕ/ር ክንደያ ገ/ሒወት፣ ደ/ር ሓጎስ እና አልማዝ ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ባቋቋመው ኮንፈረንስ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት፣ መስራቾቹ አይወክሉንም ያሏቸውን ተሿሚዎች የማንሳት መብት አላቸው ብለዋል፤ ማንኛውም አካል በጊዜያዊ አስተዳደሩ የመደበውን ተወካይ ተሿሚ ይቀየርልኝ ካለ በሌላ መተካት ይችላል ሲል በኮንፈረንሱ ተስማምነታል ሲሉ ጠቁመዋል።  

የትግራይ ሰራዊት በካቢኔው ውስጥ 5 ተወካዮች አሉት፣ የትግራይ ምሁራንም 5 ተወካዮች አሏቸው መቀየር ከፈለጉ ተወካዮቻቸውን በማንሳት በሌላ መተካት ይችላሉ ሲሉ ገልጸዋል።

በዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሁነው በማገልገል ላይ ያሉትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ አምስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላትን ከስልጣን አንስቻለሁ ሲል ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በክልሉ ስርአት አልበኝነት እንዲፈጠር እየሰራ ነው ባለው የእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “የህወሓት ቡድን ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ” ሲል ማስጠንቀቁንም ዘገባችን አካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button