ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የእስራኤል_ሄዝቦላ ጦርነት መባባሱን ተከትሎ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተጋረጠባቸው አደጋ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/ 2017 ዓ/ም፦ በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ በሊባኖስ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ገለጸ።

በእስራኤል እና በፍልስጤሙ ሃማስ መካከል በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ግጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እየተፈጸሙ ያሉ የአየር ጥቃቶች እና የተጠናከሩ ወታደራዊ እርምጃዎች በአካባቢው ነዋሪዎች እና ስደተኞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመደገፍ አልሞ የተቋቋመው “የእኛ ለእኛ በስደት” ግብረሰናይ ድርጅት መስራች እና ዳይሬክተር የሆኑት ባንቺ ይመር ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት “አሁን ላይ በሊባኖስ በየእለቱ በተለይም እኩለ ለሊት ላይ የአየር ድብደባዎች እየተፈጸሙ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም “ስደተኞቹ አከባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ብዙውን ጊዜ የሚመጣው ከ20 እስከ 40 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በመሆኑ ብዙ ስደተኞች ለማምለጥ እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል” ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች አሰሪዎቻቸው አባረዋቸው ያለ መጠለያ እንደሚገኙ ተነግሯል። 

ዳይሬክተሯ በበኩላቸው “አንዳንድ አሰሪዎች ስደተኞቹ ላይ በራቸውን ቆልፈው ከሀገር ሸሽተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ስደተኞቹ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ትተዋቸው ሄደዋል።” ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በብዛት የሚኖሩባቸው እንደ ሳብራ፣ ዳሂዬ እና ሃዳት ያሉ አካባቢዎች በግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ይጠቀሳሉ ሱሉም ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የ”እኛ ለእኛ በስደት” ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት እሙ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ባላቸው ተመጣጣኝ የቤት ኪራይ ዋጋ የተነሳ በስደተኞች ተመራጭ የሆኑት እነዚህ አከባቢዎች በሄዝቦላ ታጣቂዎች መገኘት ምክንያት የጥቃት ኢላማ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

“ኢትዮጵያውያን እነዚህን ሰፈሮች የሚመርጡት ዝቅተኛ የኑሮ ወጪ ስላላቸው እና በርካቶች አስፈላጊ የሆኑ ትክክለኛ ሰነድ ስለሌላቸው ከፖሊስ ዕይታ ለመከለል ነው።” ያሉት እሙ አሁን ላይ ግን ስደተኞቹ የማያቋርጥ የአየር ድብደባ ስጋት ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አክለውም “አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጓደኞቻቸው ቤት ጥገኝነት እየፈለጉ ነው፣ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ወታደራዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከሌሎች አምስት ወይም ስድስት ሰዎች ጋር ታጭቀው እየኖሩ ናቸው::”  ያሉ ሲሆን ምንም እንኳን አብዛኞቹ ከሌሎች ጋር ጊዜያዊ መጠለያ ማግኘት ቢችሉም አንዳንዶቹ፣ መንገድ ላይ ለመተኛት እንደሚገደዱ ተናግረዋል።

ግጭቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር አከባቢዎች ለቀው እንዲሸሹ  አስገድዷቸዋል የተባለ ሲሆን ከጥቅምት 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከ150,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል። 

በተለይም ህጋዊ እውቅና የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች በዚህ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።

ባንቺ በአደጋ ጊዜ የሚሰጡ ድጋፎች በተዳከሙበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተጨማሪ ተግዳሮቶች እየገጠሙዋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ባንቺም ሆኑ እሙ የሊባኖስ ዜጎች ለመጠለያ እና ለእርዳታ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች ስደተኞች ግን በተደጋጋሚ እንደሚገለሉ ጠቁመዋል።

እሙ “ከዚህ በፊት ለስደተኞች ክፍት የነበሩ አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት አሁን የሚረዱት የሊባኖስ ዜጎችን ብቻ ነው” ያሉ ሲሆን ይህም በእርዳታ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶችን ፈጥሯል ብለዋል።

“የሊባኖስ መንግስት ት/ቤቶቹን እና አንዳንድ የመንግስት ሰፋ ያሉ ቦታዎችን ከዜጋው ውጪ ስደተኛው እንዳይገባበት ከልክሏል። ገብተው ራሱ መጠቀም አትችሉም ተብለው የተባረሩበት ሁኔታ አለ::” ሲሉ ባንቺ እየጨመረ የመጣውን አድልዎ ጠቅሰዋል።

ቀውሱ በተባባሰበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረቶች መጀመሩን አስታውቋል።

በሊባኖስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመጠለያ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን እና የእርዳታ የስልክ መስመር መዘርጋቱን ባንቺ ገልጸዋል።

ኤምባሲው ዜጎቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየመዘገበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ትናንት መስከረም 28/2016 ዓ.ም. 51 ኢትዮጵያውያን በተሳካ ሁኔታ ወደ ሃገራቸው  ተመልሰው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል ስንል መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button