ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በምዕራብ ጎጃምና አዊ ዞን በርካታ አከባቢዎች በከባድ መሳርያ የታገዙ ውጊያዎች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/ 2017 ዓ/ም፡- በአማራ ክልል፤ በምዕራብ ጎጃምና በአዊ በሔረሰብ ዞን ስር በሚገኙ በርካታ አከባቢዎች በከባድ መሳርያ የታገዙ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና መቀመጫ የሆነችው የፍኖተሠላም ከተማ ነዋሪ እንደገለጹት፤ ካለፈው ሳምንት ሀሙስ ጀምሮ በከባድ መሳርያ የታገዘ ውጊያ ሲደረግ እንደነበረ ገልጸዋል።

“ይሄን ሁለት ሶስት ቀን የከባድ መሳርያ ፍንዳታዎችን ስንሰማ ነበር። ተኩስም ቅልጥ ያለ ነበረ” ያሉት ነዋሪው ቅዳሜ ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም. የፋኖ ኃይሎች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የተኩሱ እሩምታ ረገብ ብሎ እንደነበረ ገልጸዋል።

ይሁንና ከትናንት እሁድ ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች ተመልሰው ወደ ከተማዋ ለመግባት በሶስት አቅጣጫ ውጊያ መክፈታቸውን ተከትሎ በአከባቢው ያለው ውጥረት ማገርሸቱን ነዋሪው አክለው ገልጸዋል።

ሌላኛዋ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፍኖተሰላም ነዋሪ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በከተማዋ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ከባድ ውጊያ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

“ሁለቱም ኃይሎች ከተማው ውስጥ ገብተዋል። የከተማ ውጊያ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። ሁላችንም ቤት  ታሽገን ተቀምጠናል። የሚሆነውን እየተጠባበቅን ነው።” ያሉት ነዋሪዋ እየተደረገ የሚገኘው ውጊያ ከባድ በመሆኑ የበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት ሊያልፍ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከፍኖተ ሰላም በተጨማሪ በጅጋ፤ በቡሬ እና በቲሊሊ አከባቢዎችም በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ሃይሎች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ማገርሸታቸውን ነዋሪዎች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ አረጋግጠዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአማራ ክልል በአዊ በሔረሰብ ዞን በምትገኘው ቲሊሊ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ግለሰብ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከባለፎው ሳምንት ሀሙስ ጀምሮ በከተማዋ ውጊያ ሲደረግ እንደነበረ ገልጸዋል።

“ከሐሙስ ጀምሮ ከባድ የተኩስ እሩምታዎችን እና የከባድ መሳርያ ድምጾችን ስንሰማ ነበር። አመጣጡም ለየት ያለ አስፈሪ ነበር።” ያሉት ነዋሪው በከተማዋ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ከተማዋን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ከተማዋ በፋኖ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቷንና ውጊያው ረገብ ማለቱን ጠቁመዋል።

ነዋሪው አክለውም ከቲሊሊ በተጨማሪ በጅጋ እና በቡሬ ከተሞችም ውጊያዎች ስለመደረጋቸውና እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ስለመቆማቸው ከቤተሰቦቻቸው መስማታቸውን አስረድተዋል።

በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች  ከመስከረም 23/ 2016 ዓ.ም. አንስቶ በመላው የአማራ ክልል አከባቢዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እቀባ ላልተወሰነ ጊዜ መታወጁን ተከትሎ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው በጎንደር ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ግለሰብ በበኩላቸው ከከተማ ከተማ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ መቆማቸውን ገልጸው፤ “ዘመቻ 100 ተራሮች” የተሰኘ ልዩ ኦፕሬሽን በፋኖ ሃይሎች መጀመሩን እንደሰሙና ይህም በአከባቢው ያለውን ውጥረት እንዲባባስ እንዳደረገው ጠቁመዋል። 

የአማራ ክልል መንግስት እና መከላከያ ሠራዊት ባሳለፍነው ሳምንት በክልሉ ሕግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቋል።

የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “በክልሉ ሁከት እና ብጥብጥን ለማስቆም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ችግር በሚፈጥሩ የታጠቁ ሀይሎች እና በመንግስት መዋቅር ላይ በሚገኙ አካላት እርምጃ መወሰድ መጀመሩን” ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች አገርሽተዋል።

ከዚህ ቀደም በመስከረም 22/2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል፤ ጎንደር ከተማ ዙርያ በሚገኙ አከባቢዎች “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ተፈጸሙ በተባለ በከባድ መሳሪያ የታገዙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 20 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከተገደሉት በተጨማሪ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 3 ግለሰቦችም ቆስለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button