አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1/ 2017 ዓ/ም፦ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በተባባሰበት አማራ ክልል፤ መስከረም 25/2017 ዓ.ም በፀደይ እና በአቢሲኒያ ባንክ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅርንጫፎች ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ በታጣቂዎች’ መዘረፉ የባንኮቹ ሥራ አሥኪያጆች አስታወቁ።
የአቢሲኒያ ባንክ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅርንጫፍ ኦፕሬሽን ሥራ አሥኪያጅ ዘውዱ ቀና እንደገለጹት መስከረም 25 ከቀኑ 11:30 ሰዓት አካባቢ “ታጣቂ ኃይሎች ገብተው እገታ እንደፈፀሙባቸው” ተናግረዋል።
በወቅቱ ባንኩ ለግሸን አመታዊ በዓል የመጡ በርካታ ተገልጋዮችን ሲያስተናግድ መቆየቱን ጠቅሰው “ታጣቂዎቹ ደብድበው እና አስፈራርተው ካዝናውን ካስከፈቱ በኋላ ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾን ገንዘብ ዘርፈው መሄዳቸውን ገልጸዋል” ሲል አሚኮ ዘግቧል።
የፀደይ ባንክ የግሸን ደብረ ከርቤ ሥራ አሥኪያጅ አማረ ማሞ በበኩላቸው ከለሊቱ 5:30 ሰዓት ላይ በታጣቂዎች ከቤታቸው ታግተው መወሰዳቸውን እና ባንኩ ሲደርሱም ዘበኞቹ ታግተው እንደጠበቋቸው ገልጸዋል።
“ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ ታጣቂዎች በቦታው እንደነበሩ” የሚገልጹት ሥራ አሥኪያጁ “ካዝናውን አስፈራርተው እና ደብድበው ካስከፈቱ በኋላ ከ 4 ሚሊዮን 813 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በማዳበሪያ ይዘው መሄዳቸውን” ገልጸዋል ተብሏል።
ሲሄዱም መረጃ ቢያወጡ በገዛ ሕይዎታቸው እና በቤተሰባቸው እንደፈረዱ በማስጠንቀቅ መኾኑንም ሥራ አሥኪያጆቹ ተናግረዋል።
አቢሲኒያ ባንክ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የሚሄደውን አማኝ እንዲያገለግል በሚል ወደ ስፍራው እንዲሄድ የጋበዘችው ቤተክርስቲያኗ መሆኗን የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አሥኪያጅ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፍራው ጠቅሰው ቤተክርስቲያኗ በተፈፀመው የዝርፊያ ድርጊት ማዘኗን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከአንድ አመት በላይ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በተለይ በዚህ ሰሞን ተባብሶ ቀጥሏል። ባሳለፍነው ሳምንት በምዕራብ ጎጃምና አዊ ዞን በርካታ አከባቢዎች በከባድ መሳርያ የታገዙ ውጊያዎች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና መቀመጫ በሆነችው በፍኖተሠላም ከተማ፣ በጅጋ፤ በቡሬ እና በቲሊሊ አከባቢዎች በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ሃይሎች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ማገርሸታቸውን ነዋሪዎች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ አረጋግጠዋል።
በመስከረም 22/2017 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ዙርያ በሚገኙ አከባቢዎች “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ተፈጸሙ በተባለ በከባድ መሳሪያ የታገዙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 20 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከተገደሉት በተጨማሪ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 3 ግለሰቦችም ቆስለዋል።አስ