ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከልን  (ካርድ)  አገደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/ 2017 ዓ/ም፦ የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) “ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባው፣ ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ መሰማራቱ” በመረጋገጡ ከሥራው መታገዱን አስታወቀ።

አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የሆነው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ከባለሥልጣኑ ሕዳር 3 ቀን 2017 በተላከለት ደብዳቤ መታገዱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

ከካርድ በተጨማሪም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (AHRE)  የተሰኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት በባለስልጣኑ መታገዱ ሪፖርቶች አመላክተዋል።

ካርድ ለመታገድ የተሰጠው ምክንያት “ከእውነታው የራቀ መሆኑን” አበክሮ በመግለጽ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እግዱን ለመጣል እንደ ምክንያት የገለጸው የምርመራ ሒደት ስለመከናወኑ ድርጅቱ ምንም ዓይነት መረጃ ያልነበረው ከመሆኑም ባሻገር፣ ውሳኔው አስፈላጊ የሆኑትን ሕጋዊ አካሄዶችን አለተከተለም ብሏል።

አክሎም የምርመራ ሒደቱን ካርድ እንዲያውቅ ተደርጎ፣ በግልጽ ሒደት ድርጅቱ መሳተፍ ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም በተግባር ግን ይህ አልተደረገም ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከሉ “ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባራት ላይ እንደማይሳተፍ እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ ተቋም መሆኑን” አጽንዖት ሰጥቷል። 

ከሐምሌ 17 ቀን 2011 ጀምሮ በርካታ አዎንታዊ ሥራዎችን በመሥራት አገራዊ ፋይዳ ያላቸው አስተዋፅዖዎችን ሲያበረክት መቆየቱን በመግለጫው የገለጸው ድርጅቱ  በዚህም፣ ወጣቶችን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ለሰላምና ለእኩልነት እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ጥብቅና እንዲቆሙ የሚያስችሉ ምርምሮችን እንዲሠሩ እና ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ እየሠራ ይገኛል ብሏል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከ40 በላይ አገር ዐቀፍ እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እና በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጋር የሚደርሱ ሥራዎችን፣ የሰብዓዊ መብቶችን እሴቶች እና ዲሞክራሲያዊ ሕዝባዊ ባሕልን ለማጎልበት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን እና ስትራቴጂካዊ ሥራዎች ላይ የሰራቸው ስራዎችም ተጠቃሽ መሆነቸውን አስታውቋል።

በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ እንዲገኝ መሟገቱን መቀጠሉን የገለጸው ካርድ በአሁኑ ወቅት ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር የእግድ ውሳኔው እንዲነሳ እና የተፈጠረው አለመግባባት መፍትሔ እንዲያገኝ በትብብር መንፈስ እና ሕጉን መሠረት ባደረገ መልኩ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል። 

እግዱ እስከሚነሳ ድረስ ህጉን በመከተል ከሕጋዊና ሁሉንም አስፈላጊ የመፍትሔ አማራጭ ጥረቶች ማድረግ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል(ካርድ) በቅርቡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአመሠራረቱ ጀምሮ እስከ ሂደቱ ድረስ “ጉልህ ክፍተቶች” እንደታዩበት በመግለጽ ማስተካከያ እንዲያደርግ ፊርማ እያሰባሰበ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button