ክልሉ ቤንዚን በምሽት እንዳይሸጥ ከልክያለሁ ብሏል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 03/ 2017 ዓ/ም፦ በሲዳማ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችው ሀዋሳ የቤንዚን እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚገኝ እና ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን አሽከርካሪዎች አስታወቁ፣ ዋነኛ መንስኤው በከተማዋ ተስፋፍቶ የሚገኘው የነዳጅ ጥቁር ገበያ ሽያጭ መሆኑንም አሽከርካሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በሀዋሳ ከተማ የታክሲ ሹፌር ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
“ቤንዚን ከማደያ ውጪ ነው በስፋት እየተሸጠ የሚገኘው። እኛ ወረፋ ሰልፍ እየጠበቅን ባለንበት ወቅት ሁለት ሶስቴ እየተመላለሱ ቤንዚን የሚቀዱ መኪኖች አሉ። ሲመላለሱ በየዙሩ 50 ብር ለቀጂው ይከፍላሉ።” ያሉት አሽከርካሪው አክለውም አሁን ላይ “ቤንዚን ለመቅዳት አራት ቀናት እየፈጀባቸው” መሆኑን በመጠቆም ያለሥራ የሚያሳልፉት ጊዜ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል።
“እኔ ለምሳሌ ባለፎው ሳምንት ሀሙስ ዕለት ቀዳሁኝ። ከዛ ተመልሼ ቅዳሜ ሊነጋጋ ሲል 11:30 ገደማ አንስቶ እስከ ቀኑ 9:30 ድረስ ረጅም ወረፋ ተሰልፌ ጠበኩኝ። ሆኖም ግን አልቋል ተብዬ ሳልቀዳ ተመለስኩ። እሁድም ዝግ ነው። ሰኞም በተመሳሳይ ምድብ አልወጣላችሁም በሚል ሳልቀዳ ቀረሁ። ዛሬም በተመሳሳይ ቀድሜ በጠዋት ወረፋ ብይዝም ከእኔ በኋላ የመጡ መኪኖች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ቀድተው ሄዱ። እኔ ግን አሁንም ተሰልፌ ቆሚያለሁ።” ሲሉ ምሬታቸውን አጋርተዋል።
በተጨማሪም አሁን ላይ በከተማዋ ነዳጅ በጥቁር ገበያ በሊትር እስከ 160 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸው: “ነዳጅ የሱቅ ሸቀጥ ሆኗል።” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።
ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በሀዋሳ ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው ይሄ ነገር እየተፈጠረ ያለው የጸጥታ አካላት ትብብር ታክሎበት መሆኑን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል።
“ነዳጅ ከማደያዎች ይልቅ በየፌርማታው ነው እየተቸበቸበ የሚገኘው። ይሄን ደግሞ የጸጥታ አካላት ይቅርና ማንኛውም ነዋሪ የሚያውቀው ነገር ነው” ብለዋል።
አክለውም በአንድ ማደያ ውስጥ በነዳጅ መቅዳት ተቀጥሮ የሚሰራ ግለሰብ “የማደያ ባለቤቶች ከክልል ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው” በአንድ ወቅት ነግረውት እንደነበር አስታውሰው: ነዳጅ ሲገባ የማደያ ባለቤቶች ለክልል ባለሥልጣናት ሪፖርት እንደሚያደርጉና ወዲያውም የነዳጅ ቦቲዎች ከሃዋሳ ከተማ ወደ ሌሎች ክልሎች እንደሚሸጋገሩ ከዚሁ ግለሰብ ንግግር መረዳታቸውን አብራርተዋል።
ሌላኛው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ሹፌር የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የነዳጅ ጥቁር ገበያ ንግድ “አሳሳቢ ደረጃ የደረሰ” ሲሉ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
“በከተማችን ቤንዚን ከማደያ ይልቅ በየፌርማታው ታገኛለህ። በሃይላንድ ነው የሚሸጠው። እንዴት ይወጣል ብትለኝ አሁን ላይ አሮጌ የሆኑ የኮሮላ መኪኖች ከኋላ በኩል በእቃ ማስቀመጫቸው ላይ ሞደፊክ የሆኑ የነዳጅ ታንከር ሰርተዋል። እኔ አንዴ በአይኔ አይቻለሁ አንድ የግል መኪና የ16 ሺህ ብር ቤንዚን ቀድቶ ሲሄድ።” ያሉት አሽከርካሪው አክለውም ቤንዚን በሊትር 91 ብር የሚሸጠውን አትራፊዎች ከማደያ በ100 ብር እየተረከቡ ለቸርቻሪዎች በ110 ወይም በ120 ብር እንደሚያስረክቡና አሁን ላይ እሳቸውም ሆኑ ሌሎች በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ከአትራፊ አትራፊ አንዱን ሊትር ቤንዚን እስከ 170 ብር በሚደርስ ዋጋ እየገዙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ ምክንያትም አሁን ላይ ሥራቸውን እንደ ልብ ለመስራት እንደተቸገሩ ገልጸዋል።
“ዛሬ ለምሳሌ በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ከ20 በላይ ከሚሆኑ ማደያዎች መካከል ቤንዚን ያለው በሁለት ማለትም በግሎባል እና በተባበሩት ማደያዎች ውስጥ ብቻ ነው።” ያሉት አሽከርካሪው ይሄ ችግር እየተለመደ በመምጣቱ የተነሳ ጥቁር ገበያው ላይ ጥገኛ መሆናቸውን እና ከወጣላቸው ታሪፍ በላይ ለመጫን መገደዳቸውን ገልጸዋል።
“ከዚህ በፊት ለምሣሌ ከአሮጌ መነሃርያ ወደ ፒያሣ አስር ብር ነበር የምንጭነው አሁን ግን አንሄድም ብለን ግማሽ ድረስ 10 ብር እንጭናለን። ቤንዚን በሊትር በእጥፍ እየገዛን በታሪፉ መጫን የማይታሰብ ነው።” ብለዋል።
አያይዘውም ያለሥራ የሚያሳልፉት ግዜ መኖሩን ጠቅሰው ለቤንዚን የሚያወጡት ወጪና ገቢያቸው የማይመጣጠን እንደሆነ አመልክተዋል።
“አንዴ ምን ገጠመኝ መሰለህ 640 ብር ቀዳሁ ቀኑን ሙሉ ውዬ የሰራሁት ግን 800 ብር ነው። እና አስበው 200 ብር ለማይሞላ ትርፍ መንከራተት ከባድ ነው። በቃ መቆም ነው ያለህ አማራጭ።” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ በምሬት አስረድተዋል።
እኚሁ ግለሰብ በከተማዋ ቅጥ ያጣውን የጥቁር ገበያ መስንሰራፋት ሃይ ባይ የሚል አካል ባለመኖሩ “ተፈቅዶልናል መብታችን ነው እያሉ ቤንዚን በጀሪካን ሁሉ እያመላለሱ የሚቀዱ አሉ።” ሲሉ ጠቁመዋል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ቡርቃ ቡጡላ በበኩላቸው ችግሩ ማጋጠሙን አምነው የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በሀዋሳ ከተማ ከሚገኙት ከሃያ በላይ ማደያዎች ውስጥ ቤንዚን እያቀረቡ የሚገኙት ከሶስት ወይም ከአራት ማደያዎች እንደማይበልጡ የገለጹት ም/ሃላፊው በአቅርቦት ችግር ምክንያት እጥረት መከሰቱን ተናግረዋል።
ይህም በከተማዋ ካለው ተሽከርካሪ ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ አለመሆኑንም አመላክተዋል።
ህገ-ወጥነትን በተመለከተም የክልሉ ንግድ ቢሮ ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ከሚመለከታቸው የፖሊስ ኮሚሽን አካላት ጋር በመቀናጀት ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ቤንዚን በማታ እንዳይሸጥ መከልከሉን ገልጸዋል።
የሚቀርበውን ነዳጅም በአግባቡ እንዲሰራጭ አሽከርካሪዎች ፕሮግራም ወጥቶላቸው እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። አስ