
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12 /2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ለወታደራዊ ስልጠና በግዳጅ የሚወሰዱ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ የፍታል ከተማ ነዋሪ ተማሪዎችን እና አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎች በግዳጅ ወደ ወታደራዊ ስልጠና መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪው አክለውም የግዳጅ ምልመላ መደረግ ከመጀመሩ በፊት በፍታል ከተማ እና አካባቢው በሚገኙ ቀበሌዎች ወጣቶች ለውትድርና ስልጠና በበጎ ፈቃደኝነት እንዲመዘገቡ ማስታወቂያ መውጣቱን አስረድተዋል።
“ሆኖም ፈቃደኛ የሚሆን ሰው አለመገኘቱን ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ አካላት ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር ግለሰቦችን በግዳጅ ማፈስ ጀመሩ።” ብለዋል
“ወጣቶች በግዳጅ መያዝ የተጀመረው ባለፈው ሳምንት በኩች፣ ጎላላ እና ላሚን ጨምሮ በ19 ቀበሌዎች መሆኑን” ነዋሪው ጠቁመዋል።
“ለገበያ ስራ ወደ ፍታል ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ወጣቶች ተይዘው ወደ ፍታል ከተማ ከተወሰዱ በኋላ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች ተልከዋል፣ ከፊሉ ለመከላከያ ሰራዊት ሥልጠና ሲወሰዱ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ሚሊሻ ካምፖች አምርተዋል” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በያያ ጉለሌ ወረዳ በርካቶች “በግዳጅ መያዝን በመፍራት በወረዳው ገጠራማ አካባቢዎች ወጣቶችን ለውትድርና በማሰልጠን ላይ ከሚገኙት ከመንግስት ሃይሎች እና ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት ጭምር እየተደበቁ” እንደሆነ ገልጸዋል።
በተመሣሣይ በጅማ ዞን ሰጠማ ወረዳ የግጦሽ ቦታ ለባለሀብቶች መሰጠቱን የተቃወሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ የተጠየቀባቸው ሲሆን መክፈል የማይችሉ ከሆነ ግን ወታደራዊ ግዳጅ እንደሚጠብቃቸው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ተቃውሞውን ተከትሎ ወንድማቸውን ጨምሮ ከ20 በላይ ሰዎች በሰጠማ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ነዋሪው እያንዳንዱ እስረኛን ለማስለቀቅ ፖሊስ ከ60,000 እስከ 70,000 ብር እንደጠየቀ ገልጸው የተጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ያልቻሉት ደግሞ ወደ ጅማ ዞን ተዘዋውረው ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች እንደሚላኩ አስረድተዋል።
“ወንድሜን ከሰጠማ ፖሊስ ጣቢያ ለማስፈታት 60,000 ብር መክፈል ነበረብኝ” ያሉት ነዋሪው አክለውም በሌሎች የወረዳው አከባቢዎች ወደ ገበያ የሚሄዱ ሰዎች ሳይቀር ሚሊሻዎች እና የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ተባብረው ለወታደራዊ ግዳጅ እንደያዟቸው ጠቁመዋል።
ድርጊቱ በገጠራማ አከባቢዎች ብቻ የተገደበ ሳይሆን በከተሞች ጭምር እየተፈጸመ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ለአብነትም በአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንዲት እናት ህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም የ17 አመት ልጃቸው ጌታቸው ተድላ ሂሪጎ በመንገድ ላይ ቆሎ እየሸጠ በነበረበት ወቅት በፖሊስ መታሰሩን አስረድተዋል።
“ከቀኑ 6:30 ላይ ልጄ በአዳማ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩ ተነገረኝ። አመሻሹን ጣቢያ ስሄድ የፖሊስ መኮንኖች ልጄን ከእስር ለማስለቀቅ 30,000 ብር መክፈል እንዳለብኝ ካልሆነ ግን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንደሚላክ ነገሩኝ። እንዳለመታደል ሆኖ ያን ያህል ገንዘብ መስጠት አልችልም።” ብለዋል።
አክለውም ልጃቸው ተድላ ለእርሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው ዋና የገቢ ምንጭ እንደነበር አስረድተዋል። “ልጄ ያደገው ያለ አባት ነው። ይህን ያህል ገንዘብ ለመክፈል የሚያስችል የገንዘብ አቅም የለንም።” ብለዋል።
ተድላ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ከመዘዋወሩ አስቀድሞ ለአምስት ቀናት በፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ነበር።
“እርዳታ የማገኝበት መንገድ ቢኖር ኖሮ ልጄ እንዲመለስ እፈልግ ነበር።” ብለዋል።
በተመሳሳይ ነዋሪነታቸው በሸገር ከተማ የሆኑ ሌላኛዋ ግለሰብ በኩሬ ጅዳ ክፍለ ከተማ ወልዶ ቀበሌ የአጎታቸው ልጅ በግዳጅ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ነዋሪዋ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ከሳምንታት በፊት የአጎቷ ልጅ ከስራ ወደ ቤት ሲመለስ በጸጥታ ሃይሎች መያዙን ገልጸዋል።
“በተለምዶ ድሬ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለሦስት ሳምንታት ያህል ታስሯል። እዚያ ልንጠይቀው ስንሄድ ከእሱ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ የታሰሩ ሰዎችን አይተናል።” ያሉት ግለሰቧ አክለውም በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኘው የአጎቷ ልጅ መደበኛ ያልሆነ ክፍያ ከተከፈለ በኋላ እንደተለቀቀ አስረድተዋል።
አክለውም “ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች ዕድለኛ አልነበሩም። ህዳር 10 ቀን ዘግይቶ ሁሉም እስረኞች ወዳልታወቀ ቦታ ሲወሰዱ ተመልክተናል። የተወሰዱት ለወታደራዊ ግዳጅ መሆኑ ግልጽ ነው።” ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ ዓርብ ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ “የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ለገንዘብ ሲባል በሚካሄዱ አፈናዎች ላይ ተሳታፊ ሆነዋል” የሚለውን ክስ “መሰረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳ” እና “ስም ማጥፋት” ሲል መግለጹ ይታወሳል።
“ይህ ዓይነቱ የስም ማጥፋት ተግባር የጸጥታ አካላት የህዝቡን ሰላም ለመመለስ የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚጎዳ እና ታሪካዊ ተጠያቂነትን ጭምር የሚያስከትል ነው” ሲል መግለጫው ያትታል።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ አካላት የሚፈጸሙ አስገዳጅ አፈሳዎችን ሲገልጹ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
አዲስ ስታንዳርድ ቀደም ሲል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች በግዳጅ ለውትድርና እንዲሰለፉ ምክንያት የሆነውን “ጋቸና ሲርና” የተሰኘውን የክልል ሚሊሻ ምልመላ ሥርዓት ትግበራን መዘገቡ ይታወሳል።
በዚህ ትግበራ መሠረት አርሶ አደሮች የግብርና ቁሳቁስ ለማግኘት የሚሊሺያ ስልጠና መውሰድ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በምልመላ ወቅት ለዕስር እንደሚዳረጉ ተገልጿል። አስ