
በይስሓቅ ኢንድሪስ @Yishak_Endris
አዲስ አበባ፣ ህዳር 10/ 2017 ዓ/ም፦ የአዲስ አበባ ከተማ ግዙፍ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የንግድ ሱቆች ከአንድ ሳምንት በላይ ዝግ በመደረጋቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል አስከትሏል።
ነጋዴዎች በደረሰኝ ግብይት እንዲፈጽሙ የከተማ አስተዳደሩ ያጣው አስገዳጅ መመሪያን ተከትሎ በነጋዴዎች እና መነግስት መካከል አለመግባባት ያስከተለ ሲሆን በዚህም ምክንያት ሶቆች በመዘጋታቸው የዕለት እንጀራቸው መገደቡን አንዳንድ ነጋዴዎች እና በጫኝ- አውራጅ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ትናንት ህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ የመርካቶ አከባቢዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ በተፈጠረው ስጋት የተነሳ በርካታ ሱቆች የተዘጉ መሆኑንና ክፍት በሆኑ መደብሮች ደግሞ ምርቶች የሉም እየተባሉ መሆኑን ተገንዝቧል።
በመርካቶ ቦምብ ተራ አካባቢ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነጋዴ፤ በአከባቢው ያለው ውዥንበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸው ይሄን ተከትሎ እንቅስቃሴ መገደቡንና የዕለት ገቢያቸውም እንደቆመ ያስረዳሉ።
“ካለፈው ሳምንት አንስቶ እኔም ሆንኩ እዚህ የምታይዋቸው ነጋዴዎች ውዥንብር ውስጥ ነበርን። አንዳንዱ ንብረት ይወረሳል ይላል ሌላው አያሰሩንም ከዚህ በኋላ ይላል። በቃ ሁሉም የየራሱን አስተያየት እና ፍርሃት ነው የሚናገረው።” ያሉት ነጋዴው አክለውም በዚህ ስጋት የተነሳ በርካቶች መደብሮቻቸውን እንደዘጉ አስረድተዋል።
ሌላኛው በመርካቶ ዱባይ ተራ አከባቢ በመጋረጃ እና የሶፋ ጨርቅ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴ በበኩላቸው ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ አብዛኛው በአነስተኛ እና መካከለኛ የችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማራው ነጋዴ መደብሮቹን መዝጋቱን ይገልጻሉ።
“እቃዎቹን ስትሸጥ ደረሰኝ እይቆረጥም ምክንያቱም አብዛኛው ነጋዴ ደረሰኝ ተቆርጦለት አይደለም እቃዎችን የተረከበው። በተለያየ አግባብ ያው ይታወቃል ከተለያዩ ቦታዎች ህጋዊ የቁጥጥር ኬላዎችን ሳይቀር በተለያየ መንገድ አልፈው የሚገቡ ምርቶች ናቸው። አሁን ላይ ከአስመጪው ወይም ከኬላ እና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገቡትን እነዚህን ምርቶች በደረሰኝ መሸጥ ጀምሩ መባሉ ነው ግርግሩን የፈጠረው።” ብለዋል።
አክለውም በደረሰኝ የማይሸጡ ነጋዴዎች ላይ ከ100 ሺህ በላይ ብር ቅጣት እየተላለፈ መሆኑ ነጋዴው ሱቁን ዘግቶ እንዲቀመጥ አርጎታል ብለዋል።
ሌላኛው በአከባቢው ያገኘናቸው ነጋዴ በበኩላቸው የደረሰኝ ቁጥጥሩ ከነጋዴው በተጨማሪ ሸማቾች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ ማስተዋላቸውን ይገልጻሉ።
በመርካቶ በርካታ ሶቆች መዘጋታቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ህዳር 2 ባወጣው መግለጫ፤ በመርካቶ አካባቢ አንዳንድ ነጋዴዎች “ንብረት ሊወረስ ነው፤ ሱቃችን ሊዘጋ ነው የሚል መሰረት የሌለው ውዥንብር ውስጥ መግባታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተመልክተናል” ሲል አስታወቋል።
ውዥንብሩ የመጣው “በደረሰኝ እንዲገበያዩ የሚጠበቅባቸው ነጋዴዎች በዚህ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ በሚደረገው ሥራ” ነው ሲል የገለጸው አስተዳደሩ ይህ እንዲስተጓጎል ሆን ተብሎ የተነዛ አሉባልታ ነው ሲል ጠቁሟል።
በውዥንብሮች እና የተሳሳቱ መረጃዎች ንብረት የሚያሸሹና ሱቅ የሚዘጉ ነጋዴዎች ተገቢነት ከሌለው ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲል ያሳሰበው አስተዳደሩ “አምራች፣ አከፋፋይና ቸርቻሪ ነጋዴዎች ያለደረሰኝ መገበያየት ህገወጥ ተግባር መሆኑን በአግባቡ በመረዳት ወደ ህጋዊ መስመር ሊገቡ ይገባል” ብሏል።
ይሁን እንጂ ይህ ማሳሰቢያ ሶቆቹ እንዲከፈቱ ያደረገው ተጽዕኖ አናሳ ነው።
አዲስ ስታንዳርድ በትናንትናው ዕለት በመርካቶ ተዘዋውሮ ለመመልከት እንደቻለው በርካታ ሱቆች እና መደብሮች የተዘጉ ሲሆን በዚህም የወትሮው የንግድ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ነው። ለአብነትም ድር ተራ፣ ሚሊቴሪ ተራና ዱባይ ተራ በሚገኙ በርካታ የንግድ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተዋል።
ሥማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በኤሌክትሮኒክስ ሥራ ተሰማርተው ያገኘናቸው ነጋዴ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በአከባቢው የገቢዎች ቁጥጥር መጠናከሩን ተከትሎ በተፈጠረ ስጋት ምርቶች እንደሚደበቁ ገልጸዋል።
“ገዢ መስለው ይመጣሉ እና ያለደረሰኝ ወይም ከዋጋው በታች የምትቆርጥ ከሆነ ቅጣቱ ተግባራዊ ያደርጉብሃል” ያሉት ነጋዴው አክለውም ከህጋዊ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች “ገቢዎች ነን” የሚሉ ግን “በሙስና እና አይን ባፈጠጠ ዝርፊያ” የተሰማሩ አካላት መኖራቸውን ይገልጻሉ።
በሰዓት ንግድ የተሰማሩ ነጋዴ በበኩላቸው የደረሰኝ ቁጥጥሩን በተመለከተ መርካቶ የሚገኙ አብዛኞቹ ምርቶች በተለያዩ መንገዶች የሚገቡ ከመሆናቸው አንጻር “እንኳን ቸርቻሪው አምጪውም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።
በዚህም ምክንያት በመርካቶ የወትሮው የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ተከትሎ የእለት ገቢያቸው መቋረጡን በጫኝ- አውራጅ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች ገልጸዋል።
አዲስ ስታንዳርድ በተዘዋወረባቸው የመርካቶ ገበያዎች በርካታ በጫኝ እና አውራጅ የተሠማሩ ግለሰቦች በተዘጉ ሱቆች ግድግዳ አጠገብ በመደዳ ቆመው የተመለከተ ሲሆን የወትሮው የጫኝ እና አውራጅ ግለሰቦች የእቃ ምልልስ እና የመርካቶ ትርምስ ተቀዛቅዟል።
በዱባይ ተራ አካባቢ በጫኝ እና አውራጅ ሥራ የተሰማራ ግለሰብ በበኩሉ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጸው ሱቆች መዘጋታቸው እና ግብይት መቀነሱን ተከትሎ የዕለት ሥራውን ለመስራት መቸገሩን ገልጿል።
የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን የገለጸው ይህ ግለሰብ የዕለት ገቢው በመቋረጡ የተነሳ አሁን ላይ ለከፍተኛ ስጋት መዳረጉን ጠቁሟል።
በዱባይ ተራ በመኪኖች እና በሱቆች አጠገብ ተደርድረው ያለሥራ ቆመው አዲስ ስታንዳርድ የተመለከታቸው ሌሎች የጉልበት ሠራተኞች የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ እንዳለ ጠቅሰው ያለው ሁኔታ ዕለታዊ ገቢያቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲገደብ ማድረጉን ተናግረዋል።
አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በበኩሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ ትናንት ህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ ሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች ከመርካቶና አካባቢው ነጋዴዎች ጋር መወያየታቸውን አስታውቋል፡፡
በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ፣ የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አይዳ አወልና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በወቅቱ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ያለንግዱ ማህበረሰብ እና ያለ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት የሚታሰብ የከተማ እድገት አለመኖሩን ጠቁመዋል።
አክለውም የታክስ አሰባሰቡን ዘመናዊ ለማድረግ እና ነጋዴውን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ በበኩላቸው የነጋዴውን ጥያቄ ለመስማት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠው በአሁኑ ሰዓት ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓት እንዲፈጠር ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በበኩላቸው ነጋዴው ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር በገባንበት በአሁኑ ወቅት “ያልተገቡ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸው ተገቢ አይደለም።” ሲሉ አሳስበዋል። አስ