አዲስ አበባ፣ ጥር 6/2017 ዓ.ም፡- ቋሚ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል በሚል ስጋት ሲቀርብበት የነበረው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም ቀርቦ ጸደቀ።
በምክር ቤቱ ዛሬ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም የጸደቀው አዋጅ በከተሞች ውስጥ በመሬት ላይ እንዲሁም በመሬት ማሻሻያ እና ህንጻዎች ላይ አዲስ ቀረጥ የጣለ ነው።
በአዋጁ በተደነገገው መሰረት ለማንኛውም ንብረት የሚከፈለው ታክስ መጠን ከንብረቱ የገበያ ዋጋ ወይም ምትክ ዋጋ 25 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል፤ የመሬት አጠቃቀም መብቶች የግብር ተመን ከዓመታዊ ታክስ ከሚከፈለው መጠን ከ 0.2 በመቶ እስከ አንድ በመቶ ይደርሳል፣ በህንፃዎች እና/ወይም በመሬት ማሻሻያዎች ላይ የሚጣለው ታክስ ከታክስ እሴት 0.1 በመቶ እስከ አንድ በመቶ መካከል ሆኖ ተቀምጧል።
አዲሱ ህግ የከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች በንብረት ታክስ ገቢ እንዲሰበስቡ ይፈቅዳል።
የዕቅድ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በምክር ቤቱ ተገኝተው ለአባላቱ በሰጡት ማብራሪያ እያደገ የመጣውን የከተማ ሕዝብ ፍላጎት እና ለለህዝቡ ፍላጎት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ያለው ሀብት መካከል ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አስታውቀዋል።
“ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የከተማ ንብረት ዋጋ በበቂ ሁኔታ ታክስ እየተጣለበት ባለመሆኑ የመንግስት የገቢ ላይ እጥረትን አስከትሏል” ብለዋል፤ “ይህም ሁኔታ በከተሞች ውስጥ ያለውን ያልተጣጣመ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲሉ ገልጸዋል።
የፓርላማ አባላት በበኩላቸው ቋሚ ገቢ ባላቸው ዜጎች እና የመንግስት ሰራተኞች ላይ ከዚህ ቀደም የተጣሉ ታክሶች ሌላ ተጨማሪ ግብር እንዲከፍሉ መደረጉ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል ሲሉ አሳስበዋል።
“ሕጉ 25 በመቶ የሚሆነው የመሬት ገበያ ዋጋ ታክስ እንደሚጣልበት ይደነግጋል፤ የግብር መጠኑም በየዓመቱ እንደሚጨምር ይገልጻል” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት የፓርላማ አባሉ ባርቱማ ፍቃዱ “ይህ ህግ በግብር ከፋዮች ላይ ያለውን ሸክም ከማጤን ይልቅ አስፈጻሚው አካል ለሆነው ለግብር ሰብሳቢው ያደላ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዓመት ከሚሰበሰበው ግብር አንፃር ተጨማሪ ግብር መጣል አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።
“መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት 490 ቢሊዮን ብር ግብር መሰብሰቡን አስታውቋል፤ ይህም በበጀት አመቱ መጨረሻ ከአንድ ትሪሊየን ብር በላይ የመሰብሰብ አቅም እንዳለው ያሳያል” ያሉት ደሳለኝ ጫኔ “ይህ መጠን የመንግስት ወጪዎችን ለመሸፈን በቂ ነው” ብለዋል
ምክር ቤቱም ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል። አስ