አዲስ አበባ፣ ጥር 16/ 2017 ዓ/ም:- በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች “የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች” ፈጸሙት በተባለ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ሸባ በተሰኘች ቀበሌ ሰኞ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም በእርሻ አውድማ ላይ የነበሩ 11 ሰዎች “በመንግሥት የጸጥታ አካላት” መገደላቸውን ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
“የጸጥታ ኃይሉ ወደ አዴት እየሄደ ባለበት ጊዜ ነው መቷቸው የሄደው። በወቅቱ አውድማ ላይ ጤፍ ሲያበራዩ የነበሩና ሽቆ (ለከብት ምግብ የሚዘጋጅ የበቆሎ አገዳ) ሲሸከሙ የነበሩ አንድ ቄስን ጨምሮ 11 ሰዎች ናቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት” ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም በወቅቱ ብራ አዳማ አውራጃ የሚገኝ ተራራ ላይ ሰፍሮ የነበረው ሰራዊቱ ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ወደ አዴት እና ዋሸራ ወደ ተባሉ ስፍራዎች መሄዱን አመልክተዋል።
ግድያው የተፈፀመ ቀን እና ሰሞን በአከባቢው ከታጣቂዎች ጋራ ውጊያ አለመደረጉን የገለጹት ነዋሪው የአከባቢው ማኅበረሰብ የጥምቀት በዓል ዕለት በተፈፀመው “አሳዛኝ ክስተት” ሃዘን ውስጥ እንደገባ ተናግረዋል።
የሟቾች የቀብር ሥነ-ሥርዓት በማግስቱ ጥር 13 ቀን 2017 ሸባ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል ብለዋል።
ሌላኛው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የአከባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ጥቃቱ መፈጸሙንና ህጻናትንና የአከባቢው ነዋሪ የሆኑ አንድ ቄስ ጨምሮ 11 ግለሰቦች መገደላቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።
“እዚያው የጤፍ እርሻቸው ላይ እያሉ ነው በተኩስ እሩምታ የተገደሉት” ብለዋል።
አከባቢው በከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ሆኖ መቆየቱን የገለጹት ነዋሪው የአሁኑ ጥቃት “ምንም ውጊያ በሌለበት ሁኔታ ወደ አጎራባች መንደሮች ሲሄዱ በነበሩ “የመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ሰዎች” ላይ የተፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ግድያውን ተከትሎ አሁን ላይ በአከባቢው በተፈጠረው ስጋት የተነሳ አርሶ አደሩ መደበኛ የእርሻ ስራውን ለመከወን መቸገሩን ገልጸው በተለይም ወቅቱ ለእርሻ ስራ አስፈላጊ ከመሆኑ አንጻር ሁኔታው “አሳሳቢ” መሆኑን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ አምቻሆ ቀበሌ 30 በተባለ አነስተኛ ከተማ ሰኞ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ነዋሪዎች “የመንግሥት ወታደሮች” ናቸው ያሏቸው ኃይሎች ሰዎችን ከቤት በማስወጣት እና መንገድ ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዕለቱ ከረፋዱ 4፡30 አካባቢ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከወረዳው ዋና ከተማ ሻውራ ወደ ደልጊ እየተጓዙ እንደነበረና የአካባቢው ማኅበረሰብ የቃና ዘገሊላ በዓልን በማክበር ላይ ሳለ ጥቃት መፈጸሙን ዘገባው አመልክቷል።
አንድ የአይን እማኝ ጥቃቱ ሲፈፅም “ጥይቱ ፋታ የለውም። አንዱ ጊቢ ገብተን ሕይወታችንን ለማትረፍ ችለናል” በማለት እንዴት እንደተረፉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ወደ ዘጠነኛ ክፍል ያለፈ ልጃቸው እንደተገደለባቸው ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ አባት በበኩላቸው ልጃቸው “ሥራ ቆይቶ ሲመጣ ነው ያለምንም ምክንያት ነው የተገደለው” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
“ተኩስ ፈነዳ። ምንድን ነው ብለን ተደበቅን። በኋላ ሲረጋጋ ብንወጣ አስከሬን ወድቆ አገኘን” ስሉ እማኝነታቸውን የተናገሩት የሟች አባት፤ አስከሬን ሲያነሱ “የአንተው ልጅም ወድቋል አሉኝ፤ እኔም ልጄን አነሳሁ” ሲሉ ልጃቸው ከሟቾች ውስጥ ይሆናል ብለው እንዳልጠረጠሩ ጠቁመዋል።
ለጥቃቱ መንስኤ በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው እና እግድ የተጣለበት ሞተር ሳይሆን እንደማይቀር ነዋሪዎች ጥርጣሬያቸውን አጋርተዋል።
“‘ሞተር ለምን ታንቀሳቅሳላችሁ? እዚህ ሞተር ካለ ፋኖ አለ” ብለው በዚህ ተበሳጭተው ነው ጨፍጭፈዋቸው የሄዱት” ሲሉ አንድ ነዋሪ ገልጸዋል።
ለበዓሉ ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ከተማዋ በሞተር እየገቡ የነበሩ እና ከጥቃቱ ያመለጡ ሌላ የዓይን እማኝ በበኩላቸው “እኛ ላይ ተኩስ ጀመሩ። ሞተሩን፤ ሰዉንም ያገኙትን በሙሉ ነበር የሚመቱት” ሲሉ ተናግረዋል።
እርሳቸው ሮጠው ሲያመልጡ ሞተሩን ሲያሽከረክር የነበረው ባለትዳር ጓደኛቸው ወዲያው መገደሉን የተናገሩት እማኙ፤ ሰባት ሠዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ስድስት መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው ጥቃቱን አስመልክተው ሲናገሩ “አንዱ ልጁን ይዞ ወደ ጥምቀት ሊሄድ ሲል፤ ልጁን ነጥለው ገደሉት። ሌላኛውም ልኳንዳ አራጅ ነው፤ ጠላ ቤት አግኝተው ነው የገደሉት። አንዱም የቀን ሥራ ነው የሚሠራው። ሁሉም ምንም የሌላቸው ደሆች ናቸው፤ ንፁህ ሰው ነው የተጨፈጨፈው” ብለዋል።
የሟቾች ሥርዓተ ቀብርም ማክሰኞ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም አምቻሆ መድኃኒያለም ቤተ ክርስቲያን እንደተፈጸመ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ውጊያ ሰብአዊ ቅውስ እየደረሰ ይገኛል።
በቅርቡ አለምአቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆሪቋሪ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች በጎርጎሮሳውያኑ 2024 ኢትዮጵያ “መጠነ ሰፊ ግጭቶች እና የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት እገዳዎች” ማስተናገዷን በመጥቀስ የሰብዓዊ መብት ሁኔታውን “አስከፊ” ሲል መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።
ድርጅቱ በወቅቱ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ግጭት ባለበት አካባቢዎች እና በሀገሪቱ ሌሎች ስፍራዎች በመንግስት የጸጥታ አካላት፣ በሚሊሻዎች እና በታጣቂ ቡድኖች ከባድ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን አመልክቷል።
በተለይም በአማራ ክልል ያለው ግጭት አሳሳቢ መሆኑን ገልጾ በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች “የጦር ወንጀል” ድርጊቶች መፈጸማቸውን ገልጿል።
ሂውማን ራይትስ ዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት መረጃን ዋቢ በማድረግ የመንግሥት የጸጥታ አካላት “ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ የሆኑ ግድያዎችን፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ ማሰቃየት እና የሲቪል ዜጎች ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ” መፈጸማቸውን ጠቁሟል። አስ