ዜናዜና ትንታኔፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና ትንታኔ፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ታስረዋል የተባሉ የከረዩ አባገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያሉበት ቦታ አለመታወቁ ስጋት መፍጠሩን ቤተሰቦችና ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/ 2017 ዓ.ም፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ታህሳስ 28/ 2017 ዓ/ም “በጸጥታ ኃይሎት” ታስረዋል የተባሉ 20 የሚሆኑ የከረዩ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ያሉበት ቦታ አለመታወቁ እንዳሳሰባቸው ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

አስር የከረዩ አባገዳዎች እና አስር የሀገር ሽማግሌዎች ለስብሰባ ከመኖሪያ ቤታቸው ከወጡ በኋላ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው  እስካሁን (ለ18 ቀናት) ወዴት እንደተወሰዱ አለመታወቁን ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

አንድ የቤተሰቡ አባል እንደታሰሩ የገለጹ ምንጭ፤ በፈንታሌ ወረዳ ታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ/ም ተይዘው ወዴት እንደተወሰዱ ካልታወቁ ሰዎች በተጨማሪም ሌሎች ብርካታ ሰዎችም ለስብሰባ በሚል አንድ ላይ ካስባሰቧቸው በኋላ በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።

“የታሰሩት በርካታ ሰዎች ናቸው፤ ነገር ግን የት እንዳሉ ያለታወቁት 20 ናቸው። እስካሁን የት እንዳሉ የምናውቀው ነገር የለም። መታሰራቸውም አልተነገረንም።  ይኑሩ ይሙቱ የምናውቀው ነገር የለም” ሲል ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። 

በዕለቱ ስብሰባው ላይ የነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ለቤተሰባቸው ደውለው “አባ ገዳዎች እና ሀገር ሽማግሌዎች ከሌሎቹ  ተነጥለው መሰዳቸውን” መናገራቸውን የአንድ ሀገር ሽማግሌ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሌላ ምንጭ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። የተወሰዱት አባ ገዳዎች ድህንነት የከረዩን ማህበረሰብና ቤተሰቦች ስጋ ላይ ጥሏል ብለዋል። 

“ከተወሰዱ በኋላ በምግብ እና የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ይዝን ስንፈልጋቸው ነበር ነገር። ግን ልናገኛቸው አልቻልንም። የወረዳውን ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ስንጠይቃቸው እዚህ የታሰረ ሰው የለም ብለውናል” ሲሉ ገልጸዋል።

የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ነጋሳ (ስሙ የተቀየረ) ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያውቅ ገልጾ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎቹ የታሰሩበት ምክንያት “ለምን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት [መንግስት ሻኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን] አባላትን ለማስገባት ፍቃደኛ አልሆኑም” በሚል ምክንያት ነው ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ከአንድ ወር በፊት አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተዋጊዎችን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ አለባችሁ ወይም የገዳ ባሊ ርክክብ ስነስርዓትን ማካሄድ አትችሉም ተብለው ነበር” ብሏል።

ይህም በተደጋጋሚ እንደተነገራቸው የገለጸው ነዋሪው ነገር ግን አባ ገዳዎች ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ከመቀበል ውጭ ከቀሪዎቹ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ለኃላፊዎች በመግለጽ፤ “መንም ማድረግ ስለማንችል በዚህም ምክንያት ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረግ እዚህ የደረሰው የገዳ ሥርዓት በዚህ ምክንያት መቋረጥ የለበትም” ሲሉ መናገራቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም አባ ገዳዎቹ በወረዳው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ገልጸው አተማማኝ ፀጥታን ለማስፈን ከመንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል ብሏል።

የት እንዳሉ ከማይታወቁ አባ ገዳዎች መካከል፣ ሮባ ጂሎ ጀንቦ፣ ጉሮ ሮባ ሃንቡ እና ሃልዳንጎ ፈንታሌ የተባሉ አባቶች የሚገኙ ሲጎን  ከሀገር ሽማግሌዎች መካከለ ደግሞ አበበ አቡሎ፣ ቆንጆ ጂሎ ጎዴቲ፣ ኡመር ሮባ አያና፣ ሁሴን ቡልቱም፣ ዋሪዮ አሰቦት፣ ደደቾ ቢፍቱ ፣ ሃዌ ጂሎ እና አሮሌ ቡላ የተባሉ አባቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።

ከእነሱ በተጨማሪም ከገጠር ለገበያ የመጡትን ጨምሮ በከተማ የነበሩ 150 የሚሆኑ ሰዎች በመተሓራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እንዲሁም ሌሎች 300 ሰዎች ደግሞ መርቲ በሚባል አካባቢ ለበጎች በታጠረ ግቢ ውስጥ ታስረው መቆየታቸውን አስረድቷል።

“በ2013 የተፈጸመው የአባ ገዳዎች ግድያ ዳግም እንዳይከሰት ስጋት አለን” _ ነዋሪዎች

በ2013 ዓ/ም 14 የከረዩ አባ ገዳዎች በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ ተገድለው መገኘታቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወቃል።

በወቅቱ መንግስት በግድያው እጁ እንደሌለበት ቢያስተባብልም መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ሮይተርስ በተናጥል ባወጡት የምርመራ ሪፖርት ግድያው የተፈፀመው በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መሆኑን አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም በ2013 ዓ/ም ከተፈጸመው ግድያ የተረፉት አባ ገዳ ሃዋስ ማቶ ቦራ መጋቢት 2014 ዓ/ም “ከአማራ ክልል በመጡ ታጣቂዎች” በጥይት ተመተው መገደላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል

የአሁኑን ክስተት በተመለከተ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ “በ2013 ዓ/ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በሚቺሌ ከረዩ አባ ገዳዎች ላይ የተፈጸመው ነገር አንሁንም እንዳይከሰት ፍራቻ” እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ፖለቲካ እና የገዳ ስርዓት መለያየት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች በከረዩ አባ ገዳዎች ላይ መመላለሳቸው ነዋሪዎችን እንዳስኮረፈ ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ስታንዳርድ የወረዳውን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ይሁን እንጂ የፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሃዋስ ጨርጨር እና የወረዳው ጸጥታና አስተዳዳር ኃላፊ አቶ ከዲር ሮባ ለቢቢሲ በሰጡት አስታየት በዚህ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

የቱለማ አባ ገዳ እና የኦሮሚያ አባ ገዳ ህብረት ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ጎበና ሆላ በበኩላቸው 20 የሚሆኑ የከረዩ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች መታሰራቸውን መስማታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

“የከረዩ አባ ገዳዎች መታሰራቸውን አውቃለሁ። ግን ወዴት እንደተወሰዱ፣ በየትኛው አካል እንደታሰሩ መረጃው የለኝም። ከቤተሰብም እንዲህ አይነት ነገር አለ ያለኝም አለ” ብለዋል።

ከታሳሪ ቤተሰብ ምንም መረጃ እንዳልደረሳቸው የገለጹት አባ ገዳ ጎበና ይሁን እንጂ ከታሰሩት ውስጥ 10 ሰዎች መፈታታቸውን ከሌሎች አካላት መስማታቸውን ተናግረዋል። አስ 

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button