አዲስ አበባ፣ ጥር 1/2017 ዓ.ም፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የተዘጋጀ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፤ በሁለት ተቃውሞ እና በ አንድ ድምጸ ተአቅቦ።
የጸደቀው አዋጅ የነዳጅ አጓጓዥ ተሸከርካሪዎችን በተመለከተ ባሰቀመጠው ግዴታ መሰረት ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂ.ፒ.ኤስ (መከታተያ) እንዲገጥም ይገደዳል።
የነዳጅ ማደያዎች ያልተቆራረጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስገደድ፣ ነዳጅ በማደያ ውስጥ እያለ ያለ በቂ ምክንያት አገልግሎት ያለመቋረጥ የሚል ድንጋጌ በአዋጁ መካተቱን በምክር ቤቱ የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አይሻ ያህያ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የነዳጅ አጓጓዥ ተሸከርካሪዎችን በተመለከተ የተሸከርካሪውን ጉዞ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመከታተል እንዲቻል ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂ.ፒ.ኤስ የመግጠም ግዴታ እንዳለበት በአዋጁ ተደንግጓል ማለታቸውን ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስለጣን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ከአስመጪው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ ድረስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ አስተማማኝ እና በፍትሀዊነት ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል አዋጅ እንደሆነ ማብራራታቸውን መረጃው አካቷል፡፡
ነዳጅ መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ በአዋጁ መደንገጉን ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በአዋጁ መሠረት “የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ” ማንኛውም ሰው፤ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፤ ከዚህ በተጨማሪም የተያዘው የነዳጅ ውጤት እንደሚወረስ አዋጁ ያትታል።
የነዳጅ ምርቶችን “ሆን ብሎ” ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
የነዳጅ ምርቶች አቅርቦታቸው፣ ክምችታቸው፣ ስርጭታቸው፣ ደህንነታቸው እና ጥራታቸው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ የነዳጅ ተቋማትና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ልምድ በሚጠይቀው መሠረት በሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያግዝ አዋጅ እንደሆነም ሰበሳቢዋ መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ላይ ያላቸውን ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረባቸውን የጠቆመው መረጃው አዋጁን መሰረት አድርጎ የደንብና መመሪያዎች አወጣጥ፣ የነዳጅ ግብይትን የሚያዘገዩ ህገ- ወጥ ኬላዎች፣ ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት እና የቁጥጥር መላላት፣ የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አከባቢዎች ስለ አዋጁ ተፈጻሚነት፣ የነዳጅ ግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ፣ የነዳጅ አቅርቦት ችግር እንዲሁም በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ስለሚጣለው ቅጣት የሚመለከቱ ጥያቄዎች መቅረባቸውነ ጠቁሟል።
በነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ እና በንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በተከበሩ ወ/ሮ አሻ ያህያ ምላሽ መስጠታቸውነ አስታውቋል፡፡
በመጨረሻም በረቂቅ አዋጁ ላይ በተጨማሪነት የቀረቡት ማሻሻያዎች ተካተውበት አዋጅ ቁጥር 1363/2017 ሆኖ በ2 ተቃውሞ እና በ 1 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡ አስ