ዜናፖለቲካ

ዜና: በትግራይ ብሔራዊ ጉባኤ ተጠርቶ ግዜያዊ አስተዳደሩ እንደገና እንዲዋቀር ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ እና በምርጫ ቦርድ እውቅና ካገኙ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ “ክልሉን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደሩ በህግ በአካል ቢኖርም በተግባር ግን ፈርሷል” ሲል ገለጸ፤ “በመሆኑም ብሔራዊ ጉባኤ ተጠርቶ ግዜያዊ አስተዳደሩ እንደገና እንዲዋቀር” ሲል ጠይቋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊም ሆነ የፍትህ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል መንግስት የለም ማለት ይቻላል ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር አሉላ ሀይሉ አስታውቀዋል።

ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ትላንት ታህሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ በሶስት ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን እነዚህም የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ አዲስ እንዲቋቋም፣ የክልሉ ተፈናቃዮች ያሉበት ችግር እና የክልሉ ግዜያዊ አንድነትን የተመለከቱ ናቸው።

የፓርቲው ሊቀመንበር አሉላ ሀይሉ በመግለጫው ላይ “የክልሉ ችግር በተሻለ ሁኔታ እንዲፈታ ለማስቻል ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደገና እንዲቋቋም” ሳልሳይ ወያነ ጥሪ ያቀርባል፣ “ይህንን ለማሳካት ደግሞ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲጠራ እንጠይቃለን” ብለዋል።

አስተዳደሩ በህግ በአካል ቢኖርም በተግባር ግን የፈረሰ ነው ሲሉ የገለጹት የፓርቲው ሊቀመንበር አሉላ ሀይሉ ከተሞች ያለከንቲባ የሚተዳደሩበት ሁኔታ ነው ያለው ሲሉ በማሳያነት አቅርበዋል።

በብሔራዊ ጉባኤውም ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ሲሉ ጠይቀዋል፤ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደርም ጠንካራ ጊዜያዊ ምክር ቤት እንዲኖር ይደረግ ሲሉም አሳስበዋል።

የክልሉን ተፈናቃዮች በተመለከተ ሊቀመንበሩ “ላለፉት አራት ክረምቶች ወደ ቤታችሁ ትመለሳላችሁ እየተባሉ ሲነገራቸው የነበሩ የክልሉ ተፈናቃዮች በቀጣዩ ክረምት ወደ ቤታቸው ለመመለስ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም” ሲሉ ተችተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“በተቃራኒው የክልሉን ግዛቶች ወረው የያዙ ሀይሎች እየተጠናከሩ እና ሌሎችንም እያፈናቀሉ ይገኛሉ” ሲሉ ወንጅለዋል።

“ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች በተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ተበትነው እየኖሩ ይገኛሉ” ሲሉ የገለጹት ሊቀመንበሩ “በበርካታ መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች የምግብ እርዳታ ስላላገኙ ብቻ በረሃብ እየሞቱ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ስደተኞች “የሀገሪቱ ገንዘብ መቀየሩን ተከትሎ ወደ ባንኮች ሂደው መቀየር እንዳይችሉ የጸጥታ ስጋት እንቅፋት ሁኖባቸዋል፣ በዚህም ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል” ብለዋል።

ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው “ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስም ሆነ የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ለማስመለስ ጊዜያዊአስተዳደሩ ምንም እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም” ሲሉ ተችተዋል።

የብሔራዊ አንድነተ አጀነዳናቸው ተብለው በፓርቲያቸን የተለዩት ሁለቱ አጀንዳዎች ማለትም ተፈናቃዮችን መመለስ እና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት ለማዋል ሲባል ብቻ የሚነሱ እየሆኑ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ እንዲያውም እንደ አጀንዳነት ማንሳት ቀርቷል ብለን ነው የምናምነው ሲል ገልጸዋል።

አጀንዳው እንዲተው የተደረገው ይህንን እንዲያስፈጽም ሃላፊነት ያለበት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በአንድ የፖለቲካ ሀይል መያዙ እና ይህ አካል ቸግር ላይ ሲዎድቅ ይዞት ስለወደቀ ነው ብለዋል።

በተያዘው አመት መጀመሪያ ላይ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች የክልሉ በአሁኑ ወቅት ያጋጠመው ችግር ዋነኛ ምክንያቱ ፖለቲካዊ ስለሆነ እና ይህም ውድቀት ሊፈታ የሚችለው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች በእኩልነት የሚሳተፉበት እና ምክር ቤት ያለው የሲቪል ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ነው ሲሉ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ውድብ ናጽነት ትግራይ እና አረና መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በጋራ በሰጡት መግለጫ ይህም ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም የክልሉ አካላት እንዲተባበሩን ሲሉ መጠየቃቸው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button