ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ነፍሰጡርን፣ ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመንግስት ጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረስ አሳሰበ 

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በቀጠለው ግጭት ነፍሰጡር እናት፣ ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። 

ኮሚሽኑ በግጭት ዐውድ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የሰብአዊ መብቶች ን የሚዳሥስ የሩብ ዓመት ሪፖርት (ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም.) ይፋ አድርጓል።

በሪፖርቱ በተለይ አማራ፣ ኦሮሚያ ክልሎች፤ በርካታ ከፍርድ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ ጅምላና የተራዘመ እስራት፣ የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ እና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ሰዎችን አስሮ ማቆየት ድርጊቶች መፈጸማቸውን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አግድ ቀበሌ፣ ውሻ ጥርስ በተባለ ጎጥ በመስከረም ወር በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቤት ለቤት በመግባት “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” እንዲሁም “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል በ8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ብሏል።

ከእነዚህም መካከል 1 የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ 3 ሴቶች እና 1 ሕፃን ይገኙበታል ያለው ሪፖርቱ በተጨማሪም 2 ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዳደረሱ እና ሌሎች 6 ሲቪል ሰዎችን ይዘው እንደወሰዱና የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል ብሏል።  

በተመሳሳይ ወር በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ዒላማን ባልለየ የጦር መሣሪያ ምክንያት ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 3 ሕፃናትን ጨምሮ በ5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ድርሷል ሲሉ ኮሚስኑ አስታውቋል። 

በውጊያ የሞቱ ሰዎችን ሥርዓተ ቀብር ሲፈጽሙ የነበሩ 3 ሲቪል ሰዎች “ለምን ትቀብራላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን፣ አንዱ መስማት የተሳነው አካል ጉዳተኛ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢሰመኮ በምዕራብ ጎንደር ዞን “የብልጽግናን መንግሥት ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “ከመከላከያ ጋር ሆናችሁ ፋኖን ተዋግታችኋል” በሚል 8 ሲቪል ሰዎች ላይ በፋኖ ታጣቂዎች  ግድያ መፈጸሙንም አስታውቋል።  

በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በደጋ ዳሞት ወረዳ፣ ፈረስ ቤት ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አማን እንየው የተባለ አንድ የ4 ዓመት ሕፃን ልጅ ሲገደል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈረስ ቤት ቅርንጫፍ የሚገኝበት ሕንጻ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል ብሏል ሪፖርቱ።

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመ ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳጃ ወለል ወረዳ፣ የላሎ ገለታ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ዳግም ኢገዙ እና አቶ ጸጋ ተክሌ የተባሉ 2 ሰዎች ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ጋር “ግንኙነት አላችሁ፤ ስንቅ እና መረጃ ታቀብላላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ  በዚያው ዕለት ማለትም መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል ሲል ገልጿል።

ከሶስት ቀናት በኋላም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣  አመያ ወረዳ ኢተያ ገምባ ጀቴ፣ ኢላላ እና ጢሮ ኢላላ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች “በአካባቢው ላለው የመንግሥት ጸጥታ ኃይል ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል አቶ አለኸኝ አባተ፣ አቶ ተመቸው አርቄ፣ አቶ በለጠ ከበደ፣ አቶ ተመስጌን ተፈራ እና አቶ አስፋ ርቀው የተባሉ 5 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡

እስራትን በተመለከተም ኢሰመኮ በአማራ ክልል በየደረጃው ያሉ የክልሉ የመንግሥት አመራሮች፣ የጸጥታ ተቋማት አመራሮች እና አባላት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ የምክር ቤት አባላት፣ ነጋዴዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ በግል ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአብነት (የቆሎ) ተማሪዎች ታስረው እንደሚገኑ ገልጿል።

ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጊዜያዊ ማቆያነት /መደበኛ ያልሆኑ/ በተመረጡ 4 ቦታዎች (ዳንግላ፣ ጭልጋ (ሰራባ ወታደራዊ ካምፕ)፣ ኮንቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች) ታስረው ይገኛሉ ተብሏል።

በመጨረሻው ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ጅማሮ በማስፋት፣ መንግሥትን ጨምሮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል። 

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፤ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ አሳስቧል።

በተጨማሪም መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙት የትጥቅ ግጭቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባላት ተጠያቂ ለማድረግ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር አሳስቧል።

በግጭቶቹም በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button