ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ ከ200 በላይ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ 

አዲስ አበባ፣ ጥር 1/ 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ200 በላይ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች “በህገ ወጥ የእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል” በሚል ከአንድ ወር በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ እንደሚገኙ የታሳሪ ቤተሰቦችና ሠራተኞች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጹ።

ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ የታሳሪ ቤተሰብ እንደገለጹት፤ ሠራተኞቹ በፋብሪካው ጥቅር ጊቢ ውስጥ በዕጃቸው እያረሱ እንደ ቦቆሎ እና ሰሊጥ ማምረት ከጀመሩ ከአስር አመታት በላይ ሲሆን ይህንንም የፋብሪካው አመራሮችም ያውቃሉ።

“ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰራተኞች በእንደዚ አይነት ስራ ነው ህይወታቸውን እየደገፉ የነበሩት። አዲስ ነገር አይደለም፤ አሁን ለምን ጥፋት እንደሆነ ግልጽ አይደለም” ሲል ነዋሪው ገልጿል።

የታሰሩት ሰራተኞቹ በፋብሪካው ጊቢ ውስጥ መኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው የሚኖሩ እንደሆኑም አክለው ገልጸዋል።

ሰራተኞቹ ከታሰሩ አንድ ወር እንዳለፋቸው እና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የተለጹት ምንጩ፤ በአሁኑ ሰዓት በሱሉላ ፊንጫ 01 ቀበሌ “በሚገኘው በቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ጊቢ” ውስጥ ታስረው እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የጅምላ እስሩ የሰራተኞቹን ቤተሰብ ህይወት አሳዛኝ አድርጎታል ሲሉ የታሳሪ ቤተሰብ አባሉ ተናግረዋል። “ለዚህ የጅምላ እስር ሰለባ የሆኑት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች ናቸው። ይህም የነዚህን ሰራተኞች ቤተሰቦች ህይወት ችግር ውስጥ ከቶታል” ሲሉ ተናግረዋል። የእርሻ ስራ ላይ ከነበሩት አመራሮች መካከል ያልታሰሩ ሰዎች መኖራቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ሌላው የፋብሪካው ሰራተኛ በበኩሉ የሰራተኞቹ ንብረት “ግልጽ ባልሆነ መንገድ ተዘርፏል” ሲል ገልጿል። “በፋብሪካው መሬት ላይ ሰራተኞቹ ካመረቱት 5ሺህ ኩንታል የሚጠጉ የተለያዩ የሰብል አይነቶች ግልፅነት በጎደለው መልኩ ተዘርፏል። ምርቱ ማን እጅ እንደገባ እንኳን አይታወቅም” ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሰራተኞቹ ለስብሰባ ተፈለጋላችሁ በሚል በስብሰባ አዳራሽ ከተሰበሰቡ በኋላ “በህገወጥ መንገድ” በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል ምንጩ ተናግሯል።

በተጨማሪም የእስረኞቹ ቤተሰቦች ሲጠይቁ ኃላፊነት የሚወስድ አካል እንደሌለ የገለጸው ምንጩ “የወረዳውን አስተዳደር ስንጠይቅ ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም ይላል” ብሏል።

የፋብሪካው አስተዳደርም የወረዳውን አስተዳደር እንድንጠይቅ ነው የሚጠቁሙን በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ሀላፊነቱን የወሰደ አካል የለም ሲል ገልጿል። “የክሱ ምክንያት በቂ አይመስለኝም” ያለው ሰራተኛው “በሰራተኞቹ ላይ ሌላ ክስ ለመመስረት ምክንያት እየፈለጉ ይመስላል” ብሏል። 

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ስታንዳርድ የፋብሪካውን አስተዳደር ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አለተሳካም።

ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በተለያዩ ጊዜያት በመለዋወጪያ እቃ እጥረት ምክንያት ተዘግቷል እንደነበር አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። በተጨማሪም የፋብሪካው ንብረት በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂዎች ዘረፋ እና ውድመት እንደተፈጸመበት መዘገቡ ይታወሳል።አስ

.

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button