ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በእርዳታ እጦት እና በፖለቲካ ሽኩቻ ሳቢያ በትግራይ ክልል በሚግኙ የተፈናቃይ ማዕከላት የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው

በሞላ ምትኩ @MollaAyenew

አዲስ አበባ፣ ጥር 3/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ በዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በሚመራው ቡድን እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት  ክልሉ  የፖለቲካ  ውዥንብር ላይ ይገኛል።

ይህ አለመግባባት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ በክልሉ 99 መጠለያ ማዕከላት በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ከፍተኛ የምግብ እጥረት፣ የህክምና አገልግሎት አቅርቦት ውስንነት እና በቂ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይቀርብ እና ለከፋ ችግሮች እንዲዳረጉ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።

በተለይ ደግሞ በአድዋ፣ አዲግራት፣ ሽሬ እና አክሱም ከተሞቸ በተጨናነቁ የመጠለያ ካምፖች በሚኖሩ ተፈናቃዮች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። እነዚህ ካምፖች ከፍተኛ የምግብ እርዳታ እና የህክምና አገልግሎት እጦት ያለባቸው፣ ከረሃብ ጋር ተያይዞ በተለይ ህጻናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶች ለሞት ተጋላጭ  የሆኑበት ሁኔታ መፈጠሩን ተፈናቃዮችና አስተባባሪዎቻቸው አስታውቀዋል።

በሽሬ ከተማ የተፈናቃዮች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ወላይ በርሄ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ባለፉት ሶሰት ወራት ብቻ “ህንፃድ ማዕከል” ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል 300 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ይናገራሉ።

አስተባባሪው በየቀኑ ቢያንስ አንድ ሞት እንደሚመዘገብ ጠቁመው አንዳንድ ቀናት ደግሞ ሁለትና ሶስት ግለሰቦች በአንድ ጊዜ ሲቀበሩ ይታያል ብለዋል።

“በዚህ ረገድ በተለይ እናቶች፣ ህጻናትና አረጋውያን ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው” ሲል ወላይ ገልጿል። “የሞቱት ሰዎች በዋናነት በረሃብ እና በህክምና እጦት ነው” ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አስተባባሪው አክለውም በሽሬ ተፈናቃዮች ማዕከላት ላይ እየደረሰ ላለው ከፍተኛ ጉዳት የውሃ፣ የምግብ እና የህክምና ርዳታ እጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉ አስታውቀዋል።

“በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ምንም አይነት እርዳታ አያገኙም” ሲል የገለጸው አስተባባሪው “በሽሬ እና አካባቢው ከሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ 500ሺ ከሚጠጉት ውስጥ 40 በመቶው ብቻ እርዳታ ሲያገኙ ቆይተዋል” ሲል ገልጿል።

“የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፣ ሁኔታውን ለመቁጠር፣ ለመመዝገብ ወይም ለመፍታት ምንም ዓይነት ጥረት እየተደረገ አይደለም” ያለው አስተባባሪው “አመራሩ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ስለገባ፣ ከተፈናቃዮች አስቸኳይ ፍላጎት ይልቅ ለስልጣን ሩጫ በማስቀደሙ ነው” ችግሩን ያባባሰው ሲል አስታውቋል።

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በፕሪቶርያ የተደረሰው ስምምነት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ይመለሳሉ የሚለው ተስፋ አሁን አሁን እየደበዘዘ ነው።

በ2016 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ የተጀመረው ተፈናቃዮችን የመመለስ መርሃ ግብር ተፈጥሮ የነበረው ተስፋ በአጭር ጊዜ 56 ሺ ተፈናቃዮች  ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ በድንገት መቋረጡ ይታወቃል።

ፕሮግራሙ ከተቋረጠ በኋላ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት እና ከፍተኛ የህወሓት አባላት የተፈናቃዮቹን መመለስ መቆም ወይም ለተመላሾች የእርዳታ አቅርቦት መጓደልን በዝምታ ማለፍን መርጠዋል።

የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን እነዚህ ግለሰቦች “ከእንግዲህ ወዲህ የመምራት፣ የመወሰን ወይም መመሪያ የማውጣት ስልጣን አይኖራቸውም” ሲል በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ የደብረጽዮን ቡድን “መፈንቅለ መንግሥት” በሚል ርምጃ ክልሉን “ለማተራመስ”  በሚል እርስ ብርስ መወነጃጀል ቀጠሉ።

ፕሬዝዳንት ጌታቸው በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ ውስጥ “የህገ-መንግስታዊ አስተዳደር እጦት” ለቀጣይ ተግዳሮቶች መነሻ መሆኑን አምነው “በአመራራችን ውስጥ ያለው የውስጥ መከፋፈል ለህዝባችን በብቃት ለመደራደር እና ለመደገፍ ያለንን አቅም የበለጠ እንቅፋት አድርጎብናል” ብለዋል።

ሁለቱም ቡድኖች አንገብጋቢ ችግሮችን በጋራ ከመፍታት ይልቅ፣ ችግሮቻቸውን የበለጠ የሚያባብሱ በውስጣዊ የስልጣን ሽኩቻዎች ተጠምደዋል ሲሉም አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ ።

የክልሉ ፖልቲካ ውጥረት እየተባባስ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮች ሞት እያቫቀብ መጥቷል።  አቶ ብርሃነ ካህሳይ በዓዲግራት ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች አስተባባሪ ናቸው።

አስተባባሪው እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት 40 የሚጠጉ ግለሰቦች ህይወታቸው አልፏል። ከሟቾቹ መካከል 14 እናቶች እና 18 የሚሆኑት ደግሞ ከ18 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ይገኙበታል ሲሉ አስታውቀዋል።

“በከተማው ያሉ የስደተኛ ካምፖች በከፍተኛ  ደረጃ የተጨናነቁ፣ ጽዳትና ንፅህና የጎደላቸው፣ ንፁህ ውሃ የሌለባቸው እና ከፍተኛ የምግብም ሆነ  የህክምና አገልግሎት እጥረት ያለባቸው ናቸው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

በትግራይ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ መሰረት ከ 956 ሺ በላይ ተፈናቃዮች ያለ ምንም በቂ እርዳታ  ችግር ላይ ይገኛሉ፣  ተፈናቃዮቹ ካጋጠማቸው ፈተና አንዱ የምግብ ዋስትና እጦት መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።

አቶ ብርሃኔ አያይዘውም “ዕርዳታ እንዲወስዱ የተመደቡት እንኳን መደበኛ እና በቂ ያልሆነ ስርጭት ያጋጥማቸዋል። በተጨማሪም ከምዕራብ ትግራይ፣ ከዛላምባሳ፣ ከአዲያቦ፣ ከኢሮብ እና ከኩሎ መከዳ ለተፈናቀሉ  ከ65ሺ  በላይ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ተደራሽ አይደለም። ህክምና የሚያገኙትም ክፍያ መክፈል የሚችሉ ብቻ ናቸው።

“ሁሉም ተፈናቃዮች እርዳታ የማያግኙ ሲሆን ለአብነት በአዲግራት ከሚገኙት 65ሺ ተፈናቃዮች መካከል 65 በመቶ ብቻ ናቸው እርዳታ የሚያገኙት” ሲሉ አቶ ብርሃነ ይናገራሉ። ለምን እንደማይሰጣቸው ሲጠይቁ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት እየተቸገሩ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል ይላሉ አስትባባሪው።

አስተባባሪው አያይዘውም “የመጠለያዎች መጨናነቅ እንደ ኮሌራ፣ ወባ እና የመተንፈሻ አካላት ያሉ በሽታዎች በፍጥነት እንዲስፋፉ አድርጓል” ሲሉ የሚያብራሩት አስትባባሪው “የመሠረታዊ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች አለመኖር ቀደም ሲል የነበሩትን አሳሳቢ የጤና ሁኔታዎች የበለጠ ያባብሰዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ ካጋጠሟቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አንዱ የምግብ ዋስትና እጦት እንደሆነም ይናገራሉ፤  “ለበርካቶች የሰብአዊ እርዳታ መከልከሉ ከአካባቢው የምግብ ምርት መቀነስ ጋር ተዳምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ለህልውና በራሳቸው መንገድ ብቻ እንዲተማመኑ አድርጓል።”

በአዲግራት ከተማ በተጨናነቁ እና በቂ ሀብት ከሌላቸው የተፈናቃዮች ካምፖች ውስጥ በአንዱ የሚኖሩ የሶስት ልጆች እናት ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ቤተሰቦቻቸው ከክልልና ከፌዴራል መንግስታት እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እርዳታ ከተገለሉ በርካታ አባወራዎች መካከል አንድዋ ናቸው።

“ቤተሰቦቼ ከእርዳታ ድርጅቶች ምግብ ከሚቀበሉ ተፈናቃዮች ዝርዝር ውስጥ አይደሉም” ይላሉ አዛውንትዋ። “በመሆኑም  ከረሃብ ጋር መታገል የማያቋርጥ የዕለት ተለት የሕይወቴ ክፍል ሆኗል፣ ከዚህም በተጨማሪ  ነጻ ህክምና አለመኖሩ ሌላ ከባድ ሸክም ጨምሯል” ይላሉ።

በአድዋ ከተማ በ2016 ዓ.ም ብቻ 158 ተፈናቃዮች መሞታቸውን የገለጹት ደግሞ የትግራይ ክልል የማዕከላዊ ዞን አስተባባሪ አቶ አብረሃ ገብረሰላማ ናቸው። “የሟቾች ቁጥር ከዕለተ ወደ ዕለት እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ብዙ ሰዎች እርዳታ እየተከለከሉ በመሆናቸው ዋነኛው የሞት መንስኤ ረሃብ ነው” በሚል  ለአዲስ ስታንዳርድ የተናገሩት አስተባባሪው በአድዋ ከተተጠለሉ  88 ሺ 900 ተፈናቃዮች መካከል እርዳታ የሚያገኙተ 54 ነጥብ 2 በመቶው ብቻ  መሆናቸውን ተናግረዋል።

“በተለይ ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸው በቀላሉ ተጋላጭ ቡድኖች ላይ የሟቾችን ቁጥር እየከፋ” ነው ያሉት አስተባባሪው “በርሃብ ምክንያት እየተባባሰ የመጣው የሟቾች ቁጥርን በመስጋት ተረጂ ተፈናቃዮች ከእርዳታ ለተገለሉት ለማካፈል ከአንድ ቤተሰብ 500 ብር በፈቃደኝነት የሚያበርክቱ ቢሆንም  ይህ ህይወትን ማዳን ወይም ከረሃብ ጋር የተያያዘ ሞትን መግታት አይችልም” ይላሉ።

በአድዋ ከተማ በንግስት ሳባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሚገኙት የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የአንዱ አስተባባሪ አቶ ደስነት ፀጋይ በበኩላቸው እንደገለፁት የችግሩ ስፋት ከአቅርቦት ጋር የማይምጣጠን ነው።

“ሁኔታው አስከፊ ደረጃ ላይ ቢደርስም በክልሉ ያለው የፖለቲካ እና የጸጥታ ተግዳሮት ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ እንቅፋት ነው” ይላሉ።

ደስነት አያይዘውም የሟቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱ በተጨማሪ የምግብ፣ የመጠለያ እና የጤና አገልግሎት ባለማግኘት በርካታ ተፈናቃዮችን ለህልውና እየታገሉ መሆኑን ተናግሯል። አክለውም “አንዳንዶች ልጆቻቸውን ወደ ከተማ በመላክ ምግብ እንዲለምኑ እያደረጉ እንደሆንም አስተባባሪው ተናግረዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button