ተፋናቃዮች እያካሄዱት ያለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚደገፍ ነው ብሏል
አዲስ አበባ፣ ጥር 6/2017 ዓ.ም፡- “ይበቃል” በሚል መሪ ቃል ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ የተጀመረው በትግራይ ክልል ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች እያካሄዱት ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ የክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር እንደሚደግፈው አስታወቀ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ “ሰላማዊ ሰልፍ በመሰረቱ ትክክል እና የሚደገፍ ነው” ሲል በመግለጽ “ትልቅ እገዛ አድርጎ ስለሚመለከተው አፈፃፀሙን ከመቸውም ጊዜ በላይ በተደራጀ መንገድ ይመራል” ብሏል።
በትግራይ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች ችግራቸው እየተባባሰ እንደሚገኝ በመግለጽ ወደ ቀያችን መልሱን ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት “መሰረታዊ ሂሳቦች በአግባቡ ባለመተግበራቸው የትግራይ ህዝብ አንድነት ፈተና ላይ ወድቋል” ሲል አሳስቧል።
በስምምነቱ መሰረት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጪ የታጠቁ ሃይሎች ከትግራይ ግዛት ከሆኑ መሬቶች እንዲወጡ፣ የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ የትግራይን ህገ መንግስታዊ የግዛት አንድነት ወደነበረበት እንዲመለሰ ማድረግ፣ ተጠያቂነት ማስፈን እና ልዩነቶችን በድርድር መፍታት የሚሉት ዋና ዋና ጉዳዮቸ አልተተገበሩም ሲል አስታውቋል።
እነዚህ መሰረታዊ የስምምነቱ አስገዳጅ እና ዋነኛ ሁኔታዎች አልተተገበሩም ሲል የኮነነው መግለጫው እነዚህ ጉዳዮች አለመፈጸማቸው “ህዝባችን አስቸጋሪ እና ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ” ከቶታል” ብሏል።
“በተለያዩ ሃይሎች ስር ያለው ህዝባችን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ ነው፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ቤታቸው መመለስ ባለመቻላቸው ኢሰብአዊ ሕይወት እየኖሩ ነው” ያለው መግለጫው “ከስምምነቱ መንፈስ በተቃራኒ የትግራይ ሕገ መንግሥታዊ የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ነው” ሲል አትቷል።
የፌደራል መንግስት እስካሁን ያልተፈጸሙ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ዋነኛ ጉዳዮችን እንዲያስፈጽም በመግለጫው የጠየቀው ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በተለያዩ ሀይሎች ስር እየተሰቃዩ ያሉትን ወገኖቻችንን ነፃ እንዲያወጣ” ሲል ጠይቋል።
በተጨማሪም “ከቀያቸወ የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ያደርግ” ፣ “የትግራይ ህገመንግስታዊ የግዛት አንድነተን እንዲያሰከብር እንዲሁም ተጠያቂነት በማስፈን ህጋዊና ሞራላዊ ሃላፊነቱነ ሊወጣ የገባል” ሲል ፌደራል መንግስትን አሳስቧል።
ጊዜያዊ አሰተዳደሩ በመግለጫው የአፍሪካ ህብረት፣ የአሜሪካ መንግስት፣ የአውሮፓ ህብረትና አለም አቀፉ ማህበረሰብ የፐሪቶርያው ስምምነት በአግባቡ እንዲፈጸም፣ የትግራይ ህዝብ ከገባበት ሁለንተናዊ ቀውስ እንዲወጣ አሰፈላጊ ጫናዎችን እንዲያደረገ ሲል ጠይቋል።
በመቀለ ከተማ ሮማናት አደባባይ “ይበቃል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ ሰልፉ ያዘጋጀው “ጽላል ለምዕራብ ትግራይ” የተሰኘ የሲቪል ማህበረስ ድርጅት ሲሆን ዋነኛ አላማውም ተፈናቃዮች እያጋጠማቸው ላለው የከፋ ችግር ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ማለቱን መዘገባችን የታወሳል።
በመቀለ ከተማ ሮማናት አደባባይ የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፉ በአለምአቀፍ ደረጃ ሊካሄድ ለታሰበው “ይበቃል” ንቅናቄ አካል መሆኑም በዘገባው ተገልጿል። አስ