ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: የትግራይ ተፈናቃዮች ችግራቸው እየተባባሰ እንደሚገኝ በመግለጽ ወደ ቀያችን መልሱን ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ፣ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ነው ተብሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 5/2017 ዓ.ም፡-በትግራይ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች ችግራቸው እየተባባሰ እንደሚገኝ በመግለጽ ወደ ቀያችን መልሱን ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ መጠየቃቸው ተገለጸ።

በመቀለ ከተማ ዛሬ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፉ ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፤ በሰልፉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን በአስቸኳይ መልሱን ብለዋል።

ይበቃል በሚል መሪ ቃል ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጀው ጽላል ለምዕራብ ትግራይ የተሰኘ የሲቪል ማህበረስ ድርጅት ሲሆን ዋነኛ አላማውም ተፈናቃዮች እያጋጠማቸው ላለው የከፋ ችግር ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ተብሏል።

በመቀለ ከተማ ሮማናት አደባባይ የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፉ በአለምአቀፍ ደረጃ ሊካሄድ ለታሰበው “ይበቃል” ንቅናቄ አካል መሆኑም ተገልጿል።

ተፈናቃዮቹ በተላየዩ መንገዶች ድምጻቸውን ያሰሙ ሲሆን በሰልፉ ላይ ሲያሰሟቸው ከነበሩ መልዕክቶች መካከል “ወደቀያችን መልሱን”፣ “በኬንዳ መጠለያ መኖር ይብቃን”፣ “ትኩረት በሱዳን ለሚገኙ ስደተኞች” የሚሉት ይገኙባቸዋል።

የፅላል ምዕራብ ትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ሃላፊ አቶ ፀጋይ ተጠምቀ እንደተናገሩት “ተፈናቃዮቹ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ ቀያቸው እንመለሳለን የሚል ተስፋ ቢፈጠርባቸውም ስቃያቸው አሁንም እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።

“ሰልፉ ሰዎች በረሃብና በእርዳታ እጦት እየሞቱ መሆኑን በማጉላት፣ የካምፕ ህይወት ይበቃል የሚል ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “የሰልፉ ተሳታፊዎች የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በአስቸኳይ እንዲተገበር” የጠየቁ ሲሆን “መሪዎች የፖለቲካ ጨዋታቸውን እንዲያቆሙ እና ስምምነቱን እንዲተገብሩ እናሳስባለን” ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሰልፉ ላይ ተሳታፊ የነበረች እና ከቀየዋ ተፈናቅላ በመጠለያ የምትኖር ኪዳን ግርማይ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚደረግ ምንም አይነት እንክብካቤ እንደሌለ አፅንዖት ሰጥታ ገልጻለች። በጦርነቱ ወቅት ልጇ መጥፋቱን እና በሕይወት ለመትረፍ እየታገለች እንደሆነ ተናግራለች።

“በረሃብ እና በህክምና እጦት እየሞትን ነው” ስትል ተናግራለች፤ “መንግስትን እና አለምአቀፉን ማሀበረሰብ የምንጠይቀው ወደ ቤታችን እንዲመልሱን ነው” ብላለች።

ኪዳን በተጨማሪም ተፈናቃዮች የሚያጋጥሟቸውን አሳሳቢ ሁኔታዎች በመግለጽ በካምፑ ውስጥ ከዚህ በኋላ መቆየት እንደማትፈልግ አስታውቃለች።

በተጨማሪም “የፌደራል መንግስት እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የፕሪቶሪያን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ወደ ቤታችን የምንመለስበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹልን እንጠይቃለን፤ ስራ በመስራት እራሳችንን መደገፍ እንችላለን – በማንም ላይ ጥገኛ መሆን አንፈልግም” ብላለች።

በሰልፉ ላይ የተገኘች ሌላኛዋ ተፈናቃይ ማኣሾ ገ/እግዚአብሄር በበኩሏ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በረሃብና በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው ለሞት ቢዳረጉም ችግራቸው ትኩረት አለማግኘቱን በምሬት ገልጻለች።

“መከራችንን የሚገልጹ ቃላት ማግኘት አስቸጋሪ ነው” ብላለች “ይህም እስከ ዛሬ ከደረሰብን የከፋው ነው” ስትል ገልጻለች በጦርነቱ ወቅት ባሏን ያጣችው ማኣሾ እሷና ልጇ ከባድ ችግር እያሳለፉ እንደሚገኙ አስታውቃለች።

አክላም “ከአራት አመት በፊት የለበስነውን ልብስ አልቀየርንም እናም ምንም የሚበላ ነገር አላገኘንም፤ ብዙ ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምፑ ውስጥ እየኖሩ በረሃብ ሞተዋል” ስትል አክላለች። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button