ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በሞያሌ የ14 አመት ታዳጊ ላይ የተፈጸመው ግድያ ቁጣ አስነሳ፤ በመንግስት ጽ/ ቤቶች ላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5/ 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞና በሞያሌ ከተማ ሸዋ ባር ቀበሌ የ14 አመት ታዳጊ “በፖሊስ አባላት” መገደሉ በነዋሪዎች ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል። ታዳጊው የተገደለው ባለፈው አርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም “በፖሊስ ኃይሎች” በተተኮሰ ጥይት መሆኑ ተገጿል።

ግድያውን ተከትሎ የከተማው ህዝብ ባለፈው ቅዳሜ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሲሆን ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን ተኩስ ከፍቶ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማነጋገር የደረሰውን ጉዳት ለመለየት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የሞያሌ ከተማ ኮሚኒኬሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ “ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም በሸዋ በር ቀበሌ የተፈጸመውን ድርጊት ተከትሎ የአንድ ታዳጊ ልጅ ህይወት አልፏል” ብሏል።

በየትኛውም ድርጊት የሰው ህይወት መጥፋት የለበትም ሲል ድርጊቱን ያወገዘው ኮሚኒኬሽኑ፤ “ድርጊቱን የፈጸመ እና እጁ አለበት የተባለ የተኛውንም አካል በማጣራት ለህግ ለማቅረብ ምርመራ እየተደረገ ነው” ብሏል።

ግድያውን ተከትሎ ሰልፍ መካሄዱን የገለጸው ኮሚኒኬሽኑ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ መጠየቅ ጥፋት የለውም ብሏል። ይሁን እንጂ “ጽ/ ቤቶችን ሰብሮ በመግባት የማውደም እና በእሳት የማቃጠል” ተግባር መፈጸሙን ገልጾ ይህም ትክክል አለመሆኑንና የሰልፉን አላማ የምይወክል ነው ብሏል።

አክሎም የፖለቲካ እና ድብቅ አጀንዳ ይዞ በሰንደቀ አላማ እና ጽ/ ቤቶች ላይ ይህን ድርጊት የፈጸመ የተኛውንም አካልን  ለህግ ለማቅረብ መንግስት ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑን ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዞኑ ንጹሃን ዜጎች በጸጥታ አካላት ሲገደሉ የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም።

ከዚህ ቀደም በዞኑ ሚዮ ወረዳ ቀላ ቦነያ የተባለ የ24 አመት ወጣት “በጸጥታ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉ” ይታወቃል። ይህም ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ የነበረ ሲሆን ድርጊቱን በመፈጸም ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት የመንግስት ሚሊሻዎች መንግስት አስታውቋል። 

ከዚህ በተጨማሪም በመስከረም ወር የጸጥታ ሃይሎች በሚዮ ወረዳ ቦኩ ሉቦማ አካባቢ በአራት ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ወቅት አንድ ወጣት ሲሞት ሁለት ሰዎች ቆስለዋል።

ሚሊሻዎቹ ተኩሱን የከፈቱት መተረኞቹ “በሚሊሻዎቹ የተጠየቁትን 50 ብር የኮቴ ክፍያን ለመክፈል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው” መሆኑን ነዋሪዎች በወቅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button