ቢዝነስዜና

ዜና፡ በማዕድን ሚኒስቴር ለናሙና ወደ ውጪ የሚላኩ ማዕድናት ወደ ሀገር ቤት አለመመለሳቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/ 2017 ዓ/ም፦ ለናሙና ወደ ውጪ የሚላኩ ማዕድናት ወደ ሀገር ቤት አለመመለሳቸውን የማዕድን ሚኒስቴር የክዋኔ አዲት ሪፖርት ማሳየቱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው በ2015/16 በጀት አመት በማዕድን ሚኒስቴር ከማዕድን የሚገኝ ገቢን ማሳደጉን እና መሰብሰቡን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው ይፋ የውይይት መድረክ ላይ ነው።

የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር የሺመቤት ደምሴ በሚንስቴር መ/ቤቱ በኩል የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑን እና ለሀብት ብክነት የሚዳርግ በመሆኑ ማዕድናቱ የሚመለሱበትን ስርአት መዘርጋት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም፤ የማዕድን ሚኒስቴር በክዋኔ ኦዲት ግኝት የታዩበትን ክፍተቶች ትኩረት ሰጥቶ እንዲያርምና እንዲያስተካክል አሳስበዋል። 

ሰብሳቢዋ በኦዲት ግኝቱን መሰረት በማድረግ በሰጡት አስተያየትም በሚኒስቴር መ/ቤቱ ላይ የህግ ማዕቀፍ ክፍተት ለአብነት ፖሊሲ አለመኖሩን፣ የአለኝታና የአዋጭነት ጥናቶች በአግባቡ አለመደረጋቸውን ገልፀዋል። ስለሆነም እነዚህ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስራዎች መሆናቸውንም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ከማዕድን ዘርፉ እና ከማዕድን አምራቾች በቂ ገቢ እየተሰበሰበ አለመሆኑን ጠቁመው፤ በማዕድን ጥራት እና አለማቀፍ ተወዳዳሪ በመሆን ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም የአሰራር ስርአት መዘርጋት እንዳለበትም ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።

ዶ/ር የሺመቤት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዋን ለማበልፀግ በዋነኛነት ካስቀመጠቻቸው አምስት ዘርፎች ውስጥ አንዱ የማዕድን ዘርፍ ነው ሲሉ ገልጸው፤ የማዕድን ሚኒስቴር የታዩበትን ክፍተቶች ለማስተካከል የሚያስችል ዕቅድና እና የድርጊት መርሀ-ግብር እስከ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የፌደራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የማዕድን አዋጭነት ጥናት በተሟላ መልኩ አለመደረግ፣ የማዕድን ሀብት ሙሉ መረጃ እና ስትራቴጂ አለመኖር፣ በማዕድን ፍቃድ አሰጣጥ እና ከላይ እስከ ታች ካሉ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን በዋናነት ጠቁመዋል።

በማዕድን ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በሰጡት ምላሽም በክዋኔ ኦዲት የታዩ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል አዲስ አደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም የአዋጅ ማሻሻያ መዘጋጀቱን መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button