ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በኦሮሚያ ክልል ከ130 በላይ ሰዎች "ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ጋር ዝምድና አላችሁ" በሚል ለወራት ታስረው እንደሚገኙ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 05/ 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ኦቦራ በተሰኘ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ከ130 በላይ ሰላማዊ ሰዎች “ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት ጋር ቤተሰባዊ ግንኙነት አላች”ሁ በሚል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሰባት ወራት በላይ ታስረው እንደሚገኙ የታሳሪ ቤተሰቦች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

አቶ ደበላ ተስፋዬ የተባሉ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ወላጅ አባታቸው አቶ ተስፋዬ በያና እና እናታቸው ዶሳ ቶሌራ በናፉሮ መንደር አከባቢ በኦሮሚያ ክልል ሚኒሻዎች ተለይተው መታሰራቸውን ተናግረዋል።

አቶ ደበላ ወንድማቸው “ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ስላለው ግንኙነት መረጃ አውጣ” በሚል ወላጅ አባታቸው አቶ ተስፋዬ በያና ቅዳሜ ሚያዝያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ወላጅ አባታቸው የልጃቸውን ስልክ ቁጥር ሆነ የት እንዳለ እንደማያውቁ የገለጹት አቶ ዳባላ፤ በናፉሮ መንደር ውስጥ ከባለቤታቸው ጋራ በመሆን በግብርና ስራ እንደሚተዳደሩ እና ምንም አይነት የፖለቲካ ተልዕኮ ሳይኖርቸው ላለፉት ሰባት ወራት ያህል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

አክለውም ወላጅ እናታቸው የሆኑት ዶሳ ቶሌራ የኦሮሚያ ክልል ሚሊሻዎች ባሳለፍነው ሳምንት ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በመኖሪያ ቤታቸው በመግባት ምግብ እንድታቀርብ ጠይቀዋት ካቀረበችላቸው በኋላ ተጨማሪ ማባያ ወጥ ጠይቀዋት እንደሌላት በመናገሯ የተነሳ ወደ ኦቦራ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው እንዳሰሯት ገልጸዋል። 

በወቅቱ ወላጅ እናታቸው ከመታሰራቸው በፊት በልጆቻቸው ፊት አስጸያፊ ስድብ እና ጉንተላዎች እንዳደረሱባቸው ገልጸው እስከአሁን ድረስ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው እንደሚገኙም አመልክተዋል።

“አባቴ በደም ግፊት በሽታ ይሠቃያል። በአንድ ወቅት ህመሙ በተባባሰበት ጊዜ ህክምና እንዳያገኝ ከልክለውት ነበረ።” ያሉት አቶ ዳባላ አክለውም የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ካነጋገሩ በኋላ ወላጅ አባታቸው እንክብካቤ እና የጤና ክትትል እንዲያገኙ እንደተፈቀደላቸው ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም ወላጆቻቸውን ጨምሮ ከ130 በላይ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሰባት ወራት በላይ በኦቦራ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ አስረድተዋል።

አቶ ደረጀ ቶሎሳ የተባሉ ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው ወላጅ አባታቸው የሆኑት ቶሎሳ ሶሪ ልጃቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ውስጥ አንዱ ነው በሚል ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊሻዎች ተይዘው መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።

አክለውም ወላጅ አባታቸው ወደ ኦቦራ ፖሊስ ጣቢያ ሲወሰዱ እየተደበደቡ እንደነበረ ጠቅሰው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለሰባት ወራት ያህል እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ገልጸዋል።

“አባቴ በናፉሮ መንደር ውስጥ ያለምንም የፖለቲካ ተሳትፎ በሥነ-ሥርዓት ነው ያሳደጉን። አሁን የ67 ዓመት አዛውንት ናቸው። ታድያ በዚህ እድሜያቸው እንዴት ልጃቸውን ፈልገው ሊያመጡ ይችላሉ? ይሄ የማይታሰብ ነው።” ያሉት አቶ ደረጀ አክለውም ወንድማቸው 18 ዓመት ያለፈው እና ለገዛ ድርጊቱ ራሱ ብቻ ተጠያቂ ሊደረግ እንደሚገባ እንዲሁም አባትየው አሁን ያለበትን ቦታ እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአከባቢው አርሶ አደር የነበሩት አቶ ቀና ቶላ በኦቦራ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት በደረሰባቸው ስቃይ እና ህክምና በመከልከላቸው የተነሳ በነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም መሞታቸውን ጠቁመዋል።

አዲስ ስታንዳርድ የአሙሩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ ስለሺ ዳሳሌን እና የአሙሩ ወረዳ ፖሊስ ኃላፊ የሆኑትን ኮማንደር ዳባሳን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ላለፉት ስድስት አመታት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደጋጋሚ በሚካሄዱ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት እያለፈ ይገኛል።

ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ዶንጎሮ ወረዳ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳልአስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button