ቢዝነስዜና

ዜና: በአዳማ ከተማ በጥቁር ገበያ የነዳጅ ሽያጭ መስፋፋት ሳቢያ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙና ዋጋው መጨመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21/ 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የጥቁር ገበያ የነዳጅ ሽያጭ በመስፋፋ ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት እያጋጠማቸው መሆኑን አሽከርካሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በአዳማ ከተማ የሚኖሩ አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ፤ በነዳጅ ማደያዎች ያለው የነዳጅ አቅርቦት በጣም ውስን መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ጠቁመዋል።

“በማደያዎች በየቀኑ ያለው የቤንዚን አቅርቦት በቂ ያልሆነ ወይም ሙሉ ለሙሉ የማይገኝ በመሆኑ አሽከርካሪዎች ረጅም ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ” ብለዋል።

አክለውም  ቤንዚን ለማግኘት እስከ ሶስት ቀን አልፎ ተርፎም አንድ ሳምንት ሊወስድ እንደሚችል ጠቅሰው “ነዳጅ ከማደያዎች ውጪ በጥቁር ገበያ በስፋት እየተሰራጨ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሌላኛው በአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የባጃጅ አሽከርካሪ በበኩላቸው በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት መኖሩን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።

“ከማደያ ነዳጅ ከቀዳሁ አንድ ሳምንት ሆኖኛል” ያሉት አሽከርካሪው አክለውም ቤንዚን ለመቅዳት ከሌሉት 9:00 እስከ ቀን 10:00 ድረስ ተሰልፎ ለመጠበቅ እንደሚገደዱ ተናግረዋል።

አክለው “ነዳጅ በጊዜ ለማግኘት አሽከርካሪዎች በማደያ ጣቢያው ተሽከርካሪዎቻቸውን ለማቆየት እና ለጥበቃ ተጨማሪ ክፍያ ለመክፈል ይገደዳሉ” ሲሉ ገልጸዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አያይዘውም “አንድ ሰው ቤንዚን ሳይቀዳ አንድ ቀን ካለፈው ወይም አርፍዶ ከደረሰ ማደያው ይዘጋል እና ብቸኛው አማራጭ ነዳጅ ከጥቁር ገበያ መግዛት ነው” ሲሉ አክለዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም አንዳንድ ማደያዎች ለሁለትና ለሶስት ቀናት በቂ የሆነ ቤንዚን ያቀርቡ የነበረ ቢሆንም ይህ አሰራር አሁን ላይ መቆሙን አስረድተዋል።

አሁን ላይ ቤንዚን በጥቁር ገበያ ነዳጅ በሁለት ሊትር ከ280 እስከ 300 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት “አሽከርካሪዎች በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ በእጥፍ ጭማሪ አድርገው እየጫኑ ይገኛሉ” ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ በሀገሪቷ በቂ የነዳጅ አቅርቦት ቢኖርም በህገ ወጥ መንገድ ላልተፈቀደለት ዓላማ በመዋሉ አልፎ አልፎ እጥረት አንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል። 

በህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል። በተደረገ የቁጥጥርና ክትትል ሥራም በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት ከ226 ሺህ ሊትር በላይ ህገ ወጥ ነዳጅ እና የነዳጅ ውጤቶች ተይዘው ወደ 13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ 44 ሰዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንና እስከ ሰባት ዓመት እስራት የተቀጡ መኖራቸውንም አመላክተዋል።

ከዚህ በፊት በአማራ ክልል ያሉ አሽከርካሪዎች በተከሰተው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እና በዋጋ ንረት ምክንያት መቸገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

እንዲሁም በሲዳማ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችው ሀዋሳ የቤንዚን እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚገኝ እና ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ለዚህም ዋነኛ መንስኤው በከተማዋ ተስፋፍቶ የሚገኘው የነዳጅ ጥቁር ገበያ ሽያጭ መሆኑንም አሽከርካሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ መግለጻቸው ይታወሳል።

ጉዳዩን በተመለከተ በወቅቱ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ቡርቃ ቡጡላ በበኩላቸው ችግሩ ማጋጠሙን አምነው የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚቀርበውን ነዳጅም በአግባቡ እንዲሰራጭ አሽከርካሪዎች ፕሮግራም ወጥቶላቸው እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button