አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለስልጣናይት፤ በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን ደአወሌይ ቀበሌ በተከሰተው የትጥቅ ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ውይይት ግጭት ለማቆም እና “ሰላማዊ እና ቀጣይነት ባለው መንግድ” ለመፍታት መስማማታቸውን የሶማሊላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ስምምነቱ የተደረገው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጂጋ ከተማ በሶማሊላንድ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አብደሌ ሞሐመድ አረብ የተመራ ላዑካን ቡድን እና በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች እና ባለስልጣናት መካከል በተካሄደ ስብሰባ ላይ ነው።
የሶማሊላንድ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ፤ ውይይቱ ያተኮረው “በክልሉ ያለው አስቸኳይ የፀጥታ ስጋት” ላይ ነው ብሏል። “ሁለቱም ወገኖች ሁኔታው የበለጠ እንዳይባባስ እና ሰላምና መረጋጋትን የሚያረጋግጥ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆናቸውን” ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ታህሳስ 16/ 2017 ዓ/ም በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን ደአወሌይ ቀበሌ በተከሰተው ግጭት ከ35 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። ግጭቱ በአካባቢው በሚኖሩ ኢሳቅ እና የኦጋዴን ንዑስ ጎሳዎች መካከል ለረጅም ጊዜ በቆየው የድንበር ግጭት የተነሳ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። በዚህም ከፋፋን እና አጎራባች ዩአሌ ወረዳ የመጡ “ልዩ ፖሊስ እና ሚሊሻዎች” ደአወሌይ ቀበሌ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።
ግጭቱ ከመባባሱ በፊት አለመግባባቱን ለማስታረቅ ጥረት እየተደረገ የነበረ ሲሆን ከሀርሺን ወረዳ የመጡ ሽማግሌዎች ቀደም ሲል የተፈጠረውን ግጭት ለማሸማገል ወደ ደአወሌይ ቀበሌ ተጉዘው በአካባቢው በሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋ በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ሽማግሌዎች መገደላቸውና መታገታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። ምንጮች ግጭቱ ታህሳስ 10 ከተከሰው ግጭት የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።
ግጭቱን ለመፍታት በጅግጅጋ ተደረገው ውይይት ላይ የሶማሊላንድ ልዑካን ቡድን እንደ የፕሬዚዳንቱ ሚኒስትር ካዳር ሁሴን አብዲ ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ መሐመድ ዩሱፍ አሊ እና የሶማሊላንድ ጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኑህ እስማኤል ታኒ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትን አካቷል። በሶማሌ ክልል በኩል ደግሞ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ሁለቱም ወገኖች “እየተካሄደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ ለማስቆም” እና የጦርነቱ መንስኤዎችን ለመቅረፍ ውይይት ለመጀመር ተስማምተዋል ተብሏል። “የህብረተሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ እና ተጨማሪ የህይወት መጥፋትን ለመከላከል በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ነን” ሲል መግለጫው አክሏል። አስ