አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አክሱም ከተማ “በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ” መከልከላቸውን የገለጹ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ድርጊቱ “የትምህርት እና የሀይማኖት ነጻነታችንን ይጋፋል” ሲሉ ተቃወሙ።
ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች ተማሪ፤ “ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ወደ ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳይገቡ መከልከላቸውና ይህም ቅሬታ ማስነሳቱን” ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጻለች።
“ትምህርት ቤቶቹ የመማር መብታችንን እየነፈጉን ያሉት በሃይማኖታችን የሚጠበቅብንን ሂጃብ በመልበሳችን ነው” ያለችው ተማሪዋ “ከዩኒፎርማችን ቀለም ጋር የሚስማማ ሂጃብ እንድንለብስ ብንጠይቅም እንኳ ተከልክለናል” ብላለች።
የማዕከላዊ ዞን እስልምና ጉዳዮች ተወካይ የሆኑት ጌቱ ካሕሣይ በበኩላቸው ውዝግቡ ከሁለት ወራት በፊት መጀመሩን ገልጸው በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ ተጽፎ ተማሪዎች ትምህርት መቀጠላቸውን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደገና ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጸዋል።
አክለውም የአክሱም ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት የከተማውን ትምህርት ቢሮ በማሳተፍ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።
“ችግሩ በቅርቡ ተቀርፎ ተማሪዎች የክፍል ጓደኞቻቸውን እንዲቀላቀሉ እናደርጋለን ብለን እናምናለን” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
የአክሱም ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት ሐሙስ መስከረም 30/ 2017 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ በአራት ትምህርት ቤቶች ማለትም ወረ፣ ክንዴያ፣ አደባባይ እና መሰናዶ የሚማሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 140 የሚጠጉ ተማሪዎች ለብሔራዊ ፈተና ምዝገባ መከልከላቸውን ገልጾ ነበር።
የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ የሆኑት ሃጂ መሀመድ ካህሳይ የትምህርት ቤቶቹን ተግባር በመተቸት በተለይ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ በመከልከላቸው የተነሳ ለብሔራዊ ፈተና አለመመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።
“ሂጃብ ለሙስሊም ሴቶች ትልቅ ትርጉም ያለው የእምነታቸው መግለጫ ነው። ይህን መከልከል የእምነት ነፃነታቸውን የሚጋፋ እና መገለልን የሚያጎለብት ነው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
አክለውም እነዚህ ድርጊቶች የሃይማኖት ነፃነትን የሚያረጋግጠውን የኢትዮጵያን ህገ መንግስት የሚፃረሩ መሆናቸውን ገልጸው “የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ሂጃብ መልበስን ፖለቲካዊ ለማድረግ ሲሞክሩ መቆየታቸውን” አፅንዖት ሰጥተዋል።
“የትምህርት ተቋማት ብዝሃነትን ማክበር እና ለሁሉም ተማሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ከባቢ መፍጠር አለባቸው” ያሉት ሀጂ መሃመድ አክለውም “ትምህርት ቤቶች ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዲለብሱ ሊፈቀድላቸው ሲገባ ይህንን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተጨማሪም “ሀይማኖታዊ አልባሳት ላይ ያነጣጠሩ እርምጃዎች በማህበረሰብ መካከል መገለልን እና አለመተማመንን ሊያባብሱ እንዲሁም ማህበራዊ ትስስርን ሊያበላሹ ይችላሉ” ብለዋል።
ሀጂ መሀመድ በጉዳዩ ላይ ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑንና በቅርቡ ችግሩን እንደሚፈታ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም “ተስማሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የግለሰብ ነፃነቶችን መጠበቅ እና የጋራ መግባባትን ማሳደግን ይጠይቃል” በማለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የግለሰቦችን ነፃነት እንዲያከብሩና የአካታችነት ባህል እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል።
አዲስ ስታንዳርድ የክልሉና ዞን የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በተመሳሳይ መልኩ በቅርቡ በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኙ አራት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሙስሊም ተማሪዎች “በኒቃባቸው ምክንያት” ለሁለት ሳምንት ከትምህርት ገበታ መታገዳቸው ይታወሳል።
ጥቅምት 20/2016 የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና ስራ አስፈፃሚዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ የአ/አ ከተማ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የከተማዋ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። አስ