አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17 ዓ/ም፦ በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን ደአወሌይ ቀበሌ ትናንት ታህሳስ 16/ 2017 ዓ/ም “በአካባቢው አርብቶ አደሮች እና በመንግስት ሚሊሻዎች” መካከል በተቀሰቀሰ የትጥቅ ግጭት ከ35 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ለደህንነታቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጩ፤ ግጭቱ የተጀመረው ትናንት ረቡዕ ጠዋት፤ ከፋፋን እና አጎራባች ዩአሌ ወረዳ የመጡ “ልዩ ፖሊስ እና ሚሊሻዎች” ደአወሌይ ቀበሌ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል።
ምንጩ አክለውም፤ ግጭቱ በአካባቢው በሚኖሩ ኢሳቅ እና የኦጋዴን ንዑስ ጎሳዎች መካከል ለረጅም ጊዜ በቆየው የድንበር ግጭት የተነሳ ታህሳስ 10 ከተከሰው ግጭት የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል። በግጭቱ መነሻ ላይ የአካባቢው ሚሊሻዎች ጣልቃ መግባታቸው ከስድስት ሰዎች በላይ ሞት እንዳስከተለም ተናግረዋል።
ከሀርሺን ወረዳ የመጡ ሽማግሌዎች ቀደም ሲል የተፈጠረውን ግጭት ለማሸማገል ወደ ደአወሌይ ቀበሌ ተጉዘው እንደነበር የገለጹት ምንጩ ይሁን እንጂ ትናንት በአካባቢው በሚሊሺያዎች ጥቃት መፈጸሙና በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ሽማግሌዎች መገደላቸውና መታገታቸውን ተነግሯል ብለዋል።
ሌላኛው የአዲስ ስታንዳርድ ምንጭ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ያሉ የአርብቶ አደር ጎሳዎች ለረጅም ጊዜ የድንበር ግጭት እንደገጠማቸው በመግለጽ የተለየ አስታየት ሰጥተዋል። ምንጩ አክለው ህዳር 11 ቀን የታጠቁ ቡድኖች የዩኦሌ ወረዳ ደህንነት ቢሮ ኃላፊን ከሌሎች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች ጋር መግደላቸውን ተከትሎ ውጥረት መንገሱን ገልጸዋል።
አክለውም ታህሳስ 10 የታጠቁ ሰዎች ውጥረቱን ለመፍታት የተቋቋመውን የዕርቅ ኮሚቴ በማጥቃት አንድ ወታደር አቁሰዋል ብለዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የታጠቁ ቡድኖች በርካታ ጥቃቶችን ማድረጋቸውን የገለጹት ምንጩ፤ የትላንቱ ጥቃት ከራስ ገዟ ጎረቤት ሶማሊላንድ የተውጣጡ የታጠቁ ቡድኖችን ያካተተ ነው ብለዋል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሌላኛው ምንጭ አቶ አብዲ (ስማቸው የተቀየረ)፤ ትናንት ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂዎቹ የዮአሌ ወረዳ እና የፋፋን ዞን ሚሊሻ ኃይሎች ናቸው ብለዋል። በጥቃቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና ሚሊሻዎቹ “የአካባቢውን ማህበረሰብ መኖሪያ ቤቶች በዶዘር ማፍረሳቸው እና አንዳንድ ቤቶችን በእሳት ማቃጠላቸውን” ተናግረዋል። ብዙ ነዋሪዎች ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጠር በመፍራት ወደ ጫካ መሸሻቸውንም አክለው ገልጸዋል።
የሶማሊላንድ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር አብዳሌ ሞሃመድ አራብ “በልዩ ፖሊስ ኃይሎች” ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት አርብቶ አደር በሆኑ “ንጹሃን ላይ የተፈጸመ የጅምላ ግድያ” መሆኑን ገልጸው ድርጊቱን አውግዘዋል። ሚኒስትሩ ትናንት በወጣው መግለጫቸው፤ ድርጊቱ የሰብዓዊ መብቶችን እና የአስተዳደር መርሆዎችን በግልጽ የሚጥስ ነው ብለዋል።
ግጭቱን ለማሸማገል የተጓዙትን የሶማሊላንድ ሽማግሌዎች ማገት “ከባድ ወንጀል እና ዓለም አቀፍ መርህዎችን በግልጽ መጣስ ነው” ሲሉ “ልዩ ፖሊስን” ከሰዋል።
አክለውም “ለእነዚህ አሰቃቂ ወንጀሎች ልዩ ፖሊሱ ተጠያቂ መሆን አለበት” ብለዋል። ሶማሊላንድ ስጋቷን ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ማሳወቋን እና ጉዳዩ ላይ ለመወያየትም ቀጠሮ መያዙን አረጋግጧል።
ነገር ግን የሶማሌ ክልል መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምንም አስታየት አልሰጠም። አዲስ ስታንዳርድ የክልሉን ጸጥታ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ እንዲሁም ከሁለቱምክ ወገን በገለልተኝነት ጉዳይን ለማጣራት የደረገው ሙከራም አልተሳካል። አስ